44

1 ከዚህ በኋላ ዮሴፍ ለቤቱ አዛዥ እንዲህ ሲል መመሪያ ሰጠው፤ የሰዎቹ ስልቻ የሚይዘውን ያህል እህል በየስልቻቸው ሙላላቸው፤ የእያንዳንዱንም ገንዘብ በየስልቻው አፍ አስቀምጠው። 2 ከዚያም የብር ዋንጫዬን በታናሹ ወንድማቸው ስልቻ አፍ ከእህሉ ዋጋ ጋር ጨምረው።” አዛዡም ዮሴፍ እንዳለው አደረገ። 3 ጠዋት በማለዳ ወንድማማቾቹ አህዮቻቸውን ይዘው እንዲሄዱ ተደረገ። 4 ከከተማውም ምንም ያህል ርቀው ሳይሄዱ፣ ዮሴፍ የቤቱን አዛዥ እንዲህ አለው፤ “እነዚያን ሰዎች ቶሎ ድረስባቸውና፣ ‘በመልካም ፋንታ ክፉ የመለሳችሁት ስለ ምንድን ነው? 5 የጌታዬን የብር ዋንጫ የሰረቃችሁት ለምንድነው? ዋንጫው ጌታዬ የሚጠጣበትና ሁሉን ነገር መርምሮ የሚያውቅበት እንደሆነ አታውቁምን? ይህ ያደረሳችሁት በደል እጅግ ከባድ ነው’ ብለህ ነገራቸው።” 6 የቤቱ አዛዥም እንደደረሰባቸው፣ ልክ እንደተባለው ተናገራቸው። 7 እነርሱ ግን እንዲህ አሉት፤ “ጌታችን እንዲህ ያለ ነገር ለምን ይናገራል? እኛ አገልጋዮችህ እንዲህ ያለውን ነገር አናደርገውም። 8 ከዚህ ቀደምም በየስልቾቻችን አፍ የተገኘውን ብር ከከነዓን እንኳ መልሰን አምጥተናል፤ ታዲያ አሁን ብር ወይም ወርቅ ከጌታህ ቤት እንዴት እንሰርቃለን? 9 የጠፋው ዕቃ ከአገልጋዮችህ የተገኘበት ይሙት፤ የቀረነው የጌታችን ባሮች እንሁን።” 10 አዛዡም መልካም ነው፤ እንዳላችሁት ይሁን፤ ጽዋው የተገኘበት ሰው ባሪያዬ ይሆናል፤ የቀራችሁት ግን ከበደል ነጻ ትሆናላችሁ” አላቸው። 11 ስለዚህ በፍጥነት ስልቻዎቻቸውን አወረዱ፤ እያንዳንዱም የራሱን ስልቻ ከፈተ። 12 ከዚያም አዛዡ ፍተሻውን ከታላቁ ጀምሮ እስከ ታናሹ ድረስ ቀጠለ። በመጨረሻም ጽዋው በብንያም ስልቻ ውስጥ ተገኘ። 13 በዚህ ጊዜ ልብሶቻቸውን በሐዘን ቀደዱ፤ ሁሉም ስልቾቻቸውን በየአህዮቻቸው ጭነው ወደ ከተማይቱ ተመለሱ። 14 ይሁዳና ወንድሞቹ ወደ ዮሴፍ ቤት ሲገቡ፣ ዮሴፍ ገና ከቤቱ አልወጣም ነበር። እነርሱም በፊቱ ተደፍተው ሰገዱ። 15 ዮሴፍም፣ “ለምን እንዲህ ያለ ነገር አደረጋችሁ? እንደ እኔ ያለ ሰው ስውር ነገርን የሚያውቅበት ልዩ ጥበብ እንዳለው አታውቁምን?” ሲል ጠየቃቸው። 16 ይሁዳም፣ “ከእንግዲህ ለጌታችን ምን ማለት እንችላለን? ምንስ እንመልሳለን? እንዲህ ካለው በደል ንጹሕ መሆናችንን ማስረዳትስ እንዴት ይቻለናል? ምክንያቱም እግዚአብሔር የሠራነውን በደል ገልጦታል፤ እንግዲህ ዋንጫው የተገኘበት ሰው ብቻ ሳይሆን ሁላችንም ባሪያዎችህ እንሁን” አለ። 17 ዮሴፍም፣ “ይህንስ አላደርገውም፣ ዋንጫው የተገኘበት ሰው ብቻ የእኔ ባሪያ መሆን አለበት፤ ሌሎቻችሁ በሰላም ወደ አባታችሁ መመለስ ትችላላችሁ” አለ። 18 ይሁዳም ወደ ዮሴፍ ቀረብ ብሎ፣ “ጌታዬ ሆይ፣ እኔ አገልጋይህ አንዲት ቃል ብቻ ልናገር፣ ምንም እንኳ የፈርዖን ያህል የተከበርክ ብትሆንም እባክህ አትቆጣኝ። 19 ጌታዬ፣ ‘አባት ወይም ወንድም አላችሁ?’ ብሎ አገልጋዮቹን ጠይቆ ነበር። 20 እኛም፣ ‘አዎን ሽማግሌ አባት አለን፤ አባታችንም በስተርጅና የወለደው ትንሽ ልጅ አለው፣ ወንድምዬው ሞቶአል፣ ከአንድ እናት ከተወለዱት ልጆች መካከል የተረፈው እርሱ ብቻ ነው፤ አባቱም በጣም ይወደዋል’ ብለንህ ነበር። 21 ከዚያም አንተ አገልጋዮችህን፣ ‘እንዳየው ወደ እኔ አምጡት’ አልኸን። 22 እኛም ለጌታዬ፣ ‘ልጁ ከአባቱ ሊለይ አይችልም፤ ከተለየው ደግሞ አባትዬው ይሞታል’ አልንህ። 23 አንተ ግን እኛን አገልጋዮችህን፣ ‘ታናሽ ወንድማችሁ አብሮአችሁ ወደዚህ ካልመጣ ዳግመኛ ፊቴን ዐታዩም’ አልኸን። 24 እኛም ወደ አገልጋይህ ወደ አባቴ በተመለስን ጊዜ አንተ ጌታዬ ያልኸንን ነገርነው። 25 ከዚያም አባታችን፣ ‘እስቲ ተመልሳችሁ ጥቂት እህል ሸምቱልን’ ሲለን 26 ‘መሄድ አንችልም፤ መሄድ የምንችለው ታናሽ ወንድማችን አብሮን ሲሄድ ብቻ ነው። ታናሽ ወንድማችንን ይዘን ካልሄድን በስተቀር የሰውዬውን ፊት ማየት አንችልም’ አልነው። 27 አገልጋይህ አባቴም እንዲህ አለን፤ ‘ሚስቴ ሁለት ወንዶች ልጆች እንደወለደችልኝ ታውቃላችሁ፤ 28 አንዱ በወጣበት በመቅረቱ በእርግጥ አውሬ በልቶት ይሆናል አልሁ፣ ከዚያ በኋላ ዐላየሁትም። 29 አሁን ደግሞ ይህን ልጅ ወስዳችሁ አንዳች ጉዳት ቢደርስበት ሽበቴን በመራር ሐዘን ወደ መቃብር ታወርዱታላችሁ።’ 30 እንግዲህ አሁን ልጁን ሳንይዝ ወደ አገልጋይህ ወደ አባቴ ብመለስ ሕይወቱ ከልጁ ሕይወት ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ስለሆነ፣ 31 የልጁን ከእኛ ጋር አለመኖር ሲያይ አባቴ ይሞታል። ከዚህም የተነሣ እኛ አገልጋዮችህ የአባታችንን ሽበት በመሪር ሐዘን ወደ መቃብር እናወርደዋለን። 32 እኔ አገልጋይህ፣ “ልጅህን መልሼ ሳላመጣ ብቀር ለዘላለም በደለኛ አድርገህ ቁጠረኝ’ በማለት ስለ ልጁ ደህንነት በአባቴ ፊት ራሴን ዋስ አድርጌአለሁ። 33 ስለዚህ አሁን፣ አገልጋይህ በልጁ ፋንታ የአንተ የጌታዬ ባሪያ ሆኜ እዚሁ ልቅር ልጁ ግን ከወንድሞቹ ጋር ይመለስ። 34 ልጁን ሳልይዝ እንዴት ተመልሼ ወደ አባቴ እሄዳለሁ? እባክህ በአባቴ ላይ የሚደርሰውን መከራ እንዳይ አታድርገኝ።”