43

1 አሁንም በምድሪቱ ላይ እንደጸና ነበር፤ 2 ከግብፅ ያመጡትንም እህል በልተው ከጨረሱ በኋላ፣ አባታቸው፣ “እስቲ እንደገና ወርዳችሁ፣ ጥቂት እህል ሸምቱልን” አላቸው። 3 ይሁዳ ግን እንዲህ አለው፤ “ ያ ሰው ወንድማችሁን ይዛችሁ ካልመጣችሁ ዳግመኛ ፊቴን ዐታዩም ብሎ በጥብቅ አስጠንቅቆናል፤ 4 ወንድማችን ከእኛ ጋር እንዲወርድ ከፈቀድህ ወደዚያ ሄደን እህል እንሸምትልሃለን፤ 5 እርሱን የማትልከው ከሆነ ግን እኛም ወደዚያ አንወርድም፤ ያም ሰው፣ ‘ወንድማችሁን ይዛችሁ ካልመጣችሁ ዳግመኛ ፊቴን ዐታዩም’ ብሎናል።” 6 እስራኤልም፣ “ሌላ ወንድም አለን ብላችሁ ለዚያ ሰው በመንገር ለምን ይህን ችግር እንዲደርስብኝ አደረጋችሁ?” ሲል ጠየቃቸው። 7 እነርሱም፣ “ሰውዬው ስለ ራሳችንና ስለ ቤተ ሰባችን አጥብቆ ጠየቀን፤ እንደገናም ‘አባታችሁ አሁንም በሕይወት አለ? ሌላስ ወንድም አላችሁ?’ ሲል ጠየቀን። እኛም ለጥያቄው መልስ ሰጠነው። ታዲያ፣ ‘ወንድማችሁን ይዛችሁ ወደዚህ እንድትመጡ’ እንደሚል እንዴት ማወቅ እንችል ነበር?” ብለው መለሱለት። 8 ይሁዳም አባቱን እስራኤልን እንዲህ አለው፣ “ልጁን ከእኔ ጋር ስደደው፤ እኛም በቶሎ እንሂድ፣ ይህ ከሆነ አንተም፣ እኛም፣ ልጆቻችንም አንሞትም፣ እንተርፋለን። 9 ስለ ልጁ ደኅንነት እኔ ራሴ ኃላፊ ነኝ፤ ስለ እርሱም በግል ተጠያቂ እሆናለሁ፤ እርሱንም በደኅና መልሼ ባላመጣውና እዚህ በፊትህ ባላቆመው ለዘላለም በደለኛ እኔ ልሁን። 10 ይህን ያህል ባንዘገይ ኖሮ፣ እስካሁን ሁለት ጊዜ ደርሰን መመለስ በቻልን ነበር።” 11 ከዚህ በኋላ አባታቸው እስራኤል እንዲህ አላቸው፤ “ነገሩ እንዲህ ከሆነስ ይህን አድርጉ፣ ምድሪቱ ከምታፈራቸው ምርጥ ነገሮች ጥቂት በለሳን፣ ጥቂት ማር፣ ሽቱ፣ ከርቤ፣ ተምርና ለውዝ በየስልቻችሁ ይዛችሁ ለዚያ ሰው ስጦታ ውሰዱለት። 12 በየስልቾቻችሁ አፍ ላይ የተገኘውን ብር መመለስ ስላለባችሁ፣ ዕጥፍ ገንዘብ ያዙ፤ ያ በየስልቾቻችሁ ውስጥ የተገኘው ብር ምናልባት በስሕተት የመጣ ሊሆን ይችላል። 13 ወንድማችሁንም ይዛችሁ ወደ ሰውዬው በቶሎ ሂዱ። 14 ሌላውን ወንድማችሁንና ብንያምን ይዛችሁ ለመመለስ እንድትችሉ ሁሉን የሚችል አምላክ በምሕረቱ የዚያን ሰው ልብ ያራራላችሁ። እኔ በበኩሌ ልጆቼን ካጣሁ፣ ባዶ እጄን መቅረቴ ነው።” 15 ስለዚህ ወንድማማቾቹ ገጸ በረከቱንና ዕጥፍ ገንዘብ ይዘው ከብንያም ጋር ወደ ግብፅ ለመሄድ ጉዞ ጀመሩ፤ እዚያም በደረሱ ጊዜ ዮሴፍ ፊት ቀረቡ። 16 ዮሴፍ ብንያምን ከወንድሞቹ ጋር ባየው ጊዜ የቤቱን አዛዥ፣ “እነዚህን ሰዎች ወደ ቤት ይዘሃቸው ሂድ፣ ዛሬ ቀትር ላይ አብረውኝ ስለሚበሉ አንድ ከብት እረድና አዘጋጅ” አለው። 17 አዛዡም ዮሴፍ የነገረውን አደረገ፣ ሰዎቹንም ወደ ዮሴፍ ቤት ወሰዳቸው። 18 ሰዎቹም ወደ ዮሴፍ ቤት በመወሰዳቸው ፈሩ፤ እነርሱም፣ “ወደዚህ የመጣነው ቀደም ሲል እዚህ መጥተን ስንመለስ በየስልቾቻችን ውስጥ ተመልሶ በተጨመረው ብር ሰበብ ነው። ሰውዬው ሊያስረንና ባሪያዎች ሊያደርገን አህዮቻችንንም ሊወስድ ይችላል።” 19 ወደ ዮሴፍ ቤት አዛዥ ቀርበው፣ በቤቱ መግቢያ ላይ አነጋገሩት፤ 20 እንዲህም አሉት፤ “ለመጀመሪያ ጊዜ እህል ለመሸመት ወደዚህ መጥተን ነበር፤ 21 ነገር ግን ለአዳር በሰፈርንበት ቦታ የየስልቾቻችንን አፍ ስንከፍት እያንዳንዳችን በስልቾቻችን አፍ ላይ ብራችንን ሙሉውን አገኘነው። ገንዘቡንም ይኸው መልሰን ይዘን መጥተናል። 22 አሁንም እህል መሸመት የሚሆነን ተጨማሪ ብር ይዘን መጥተናል፤ በዚያን ጊዜ ገንዘቡን በየስልቾቻቸን ውስጥ ማን መልሶ እንዳስቀመጠው ግን አናውቅም” አሉት። 23 የቤቱ አዛዥም፣ “አይዞአችሁ አትፍሩ፣ በየስልቾቻችሁ ውስጥ ያገኛችሁትን ገንዘብ የሰጣችሁ የእናንተም የአባቶቻችሁም አምላክ ነው፤ እኔ እንደሆንሁ ብሩን ተቀብያለሁ” አላቸው። ከዚያም ስምዖንን አውጥቶ አገናኛቸው። 24 የቤቱ አዛዥ ሰዎቹን ወደ ዮሴፍ ቤት አስገብቶ እግራቸውን የሚታጠቡበት ውሃ አቀረበላቸው፤ ለአህዮቻቸውም የሚበሉት ገፈራ ሰጣቸው። 25 ምሳ በዚያ እንደሚበሉ ተነገሯቸው ስለነበር፣ ዮሴፍ በቀትር ከመግባቱ በፊት እጅ መንሻዎቻቸውን ለማበርከት ተዘጋጁ። 26 ዮሴፍም ወደ ቤቱ ሲገባ የመጧቸውን ስጦታዎች አበረከቱለት፤ ወደ መሬት ዝቅ ብለውም እጅ ነሡት። 27 ዮሴፍም ስለ ደኅንነታቸው ጠየቃቸው፣ ከዚያም፣ “ሽማግሌ አባት እንዳላችሁ ነግራችሁኝ ነበር፤ ደኅና ነው? አሁንም በሕይወት አለ?” አላቸው። 28 እነርሱም መልሰው፣ “አገልጋይህ አባታችን አሁንም በሕይወት አለ፤ ደኅና ነው” በማለት ወደ መሬት ዝቅ ብለው እጅ ነሡት። 29 ዮሴፍ በዓይኑ ሲቃኝ የእናቱን ልጅ ብንያምን ዐየና፣ “ያ የነገራችሁኝ ታናሽ ወንድማችሁ ይህ ነው?” ብሎ ጠየቃቸው። ብንያምንም፣ “ልጄ እግዚአብሔር ይባርክህ” አለው። 30 ዮሴፍ ወንድሙን በማየቱ ስሜቱ በጥልቅ ስለተነካ፣ ፈጥኖ ከፊታቸው ገለል አለ፤ ሰውር ያለ ቦታም ፈልጎ፣ ዕልፍኙ ውስጥ አለቀሰ። 31 ፊቱንም ከታጠበ በኋላ ወጣ፤ ስሜቱንም በመቆጣጠር ምሳ እንዲቀርብ አዘዘ። 32 ለዮሴፍ ለብቻው ቀረበለት ለወንድሞቹም ለብቻቸው ቀረበላቸው፤ እንዲሁም ከእርሱ ጋር ለሚበሉት ግብፃውያን ደግሞ ሌላ ገበታ ቀረበላቸው፤ ምክንያቱም ግብፃውያን ከዕብራውያን ጋር አብሮ መመገብን እንደጸያፍ ይቆጥሩት ነበር። 33 ወንድማማቾቹ ከታላቁ አንስቶ እስከታናሹ እንደየዕድሜአቸው በዮሴፍ ፊት በተርታ ተቀምጠው ነበር፤ በመገረምም እርስ በርሳቸው ተያዩ። 34 ከዮሴፍ ገበታ ላይ እየተነሣ ለእያንዳንዳቸው ምግብ ሲቀርብ የብንያም ድርሻ ከሌሎቹ አምስት ዕጥፍ ነበር። እነርሱም እንዲህ ባለ ሁኔታ አብረውት ተደሰቱ እስኪረኩም ጠጡ።