42

1 በግብፅ እህል መኖሩን ሲሰማ፣ ልጆቹን እንዲህ አላቸው፤ “ለምን እርስ በርስ ትተያያላችሁ?” 2 በግብፅ አገር እህል መኖሩን ሰምቻለሁ፤ በራብ ከመሞታችን በፊት ወደዚያ ሂድና እህል ግዙልን” አላቸው። 3 ስለዚህ ዐሥሩ የዮሴፍ ወንድሞች እህል ለመግዛት ወደ ግብፅ ሄዱ። 4 ነገር ግን ያዕቆብ የዮሴፍን ወንድም ብንያምን ክፉ ነገር ይደርስበታል በሚል ፍርሃት ከወንድሞቹ ጋር አልላከውም። 5 ራቡ በከነዓንም በመበርታቱ፣ እህል ለመሸመት ወደ ግብፅ ከሄዱት መካከል የእስራኤል ልጆችም ነበሩ። 6 በዚህ ጊዜ ዮሴፍ የምድሪቱ ገዢ ነበር፣ ለአገሩ ሰዎች ሁሉ እህል የሚሸጥላቸው እርሱ ነበር። የዮሴፍ ወንድሞችም እንደደረሱ ከፊቱ ቀርበው ወደ ምድር ለጥ ብለው ሰገዱለት። 7 ዮሴፍም ወንድሞቹን ባየ ጊዜ ዐወቃቸው፣ ነገር ግን የማያውቃቸው በመምሰል በቁጣ ቃል፣ “ከየት ነው የመጣችሁት?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም፣ “እህል ለመሸመት ከከነዓን ምድር የመጣን ነን" ብለው መለሱለት። 8 ዮሴፍ ወንድሞቹን ቢያውቃቸውም እንኳ እነርሱ ግን አላወቁትም። 9 በዚህ ጊዜ ስለወንድሞቹ ያየው ሕልም ትዝ አለውና፣ “ሰላዮች ናችሁ፣ የመጣችሁት አገራችን በየትኛው በኩል ለጥቃት የተጋለጠች መሆኗን ለመሰለል ነው” አላቸው። 10 እነርሱም እንዲህ አሉት፤ “ጌታችን ሆይ፣ እንዲህስ አይደለም፤ እኛ አገልጋዮችህ የመጣነው እህል ለመሸመት ነው፤ 11 ሁላችንም የአንድ አባት ልጆች ነን፤ አገልጋዮችህም የታመንን ሰዎች እንጂ ሰላዮች አይደለንም።” 12 እርሱም መልሶ፣ “አይደለም፣ ግብፅ በየት በኩል ለጥቃት የተጋለጠች መሆኗን ለመሰለል ነው” አላቸው። 13 እነርሱ ግን መልሰው፣ “እኛ አገልጋዮችህ በከነዓን አገር ከሚኖር ከአንድ ሰው የተወለድን ዐሥራ ሁለት ወንድማማቾች ነን። ትንሹ ወንድማችን አባታችን ዘንድ ሲሆን አንዱ ወንድማችን ሞቷል። 14 ዮሴፍም እንዲህ አላቸው፤ “ነገርኋችሁ እኮ፤ ሰላዮች ናችሁ 15 ታናሽ ወንድማችሁ እዚህ እስካልመጣ ድረስ ከዚህ ንቅንቅ እንደማትሉ በፈርዖን ስም እምላልሁ፤ ማንነታችሁ የሚረጋገጠውም በዚህ ነው። 16 ከእናንተ አንዱ ሄዶ ወንድማችሁን ያምጣ፤ የተናገራችሁትም እውነት መሆኑ ተረጋግጦ ነጻ እስክትለቀቁ ድረስ የቀራችሁት እዚሁ በእስት ቤት ትቆያላችሁ፤” 17 ሁሉንም ሦስት ቀን በእስር አቆያቸው። 18 በሦስተኛውም ቀን ዮሴፍ እንዲህ አላቸው፤ “እኔ እግዚአብሔርን ስለምፈራ እንዲህ በማድረግ ሕይወታችሁን አትርፉ። 19 ታማኝ ሰዎች ከሆናችሁ፣ ከመካከላችሁ እንዱ እዚህ እስር ቤት ሲቆይ፣ የቀራችሁት ግን ለተራቡት ቤተ ሰቦቻችሁ እህል ትወስዱላቸዋላችሁ፤ 20 ታናሽ ወንድማችሁን ግን ይዛችሁ መምጣት አለባችሁ፤ በዚህም የተናገራችሁት ቃል እውነተኛነት ይረጋገጣል፤ እናንተም ከመሞት ትተርፋላችሁ።” እነርሱም ይህንኑ ለመፈጸም ተስማሙ። 21 እርስ በርሳቸውም እንዲህ ተባባሉ፤ “በእርግጥ በወንድማችን ላይ ስላደረስነው በደል ቅጣታችንን እየተቀበልን ነው። እርሱ እንደዚያ ተጨንቆ ስለ ሕይወቱ ሲማጠነን፣ እኛ አልሰማነውም ነበር፤ ይህ መከራ የደረሰብንም በዚሁ ምክንያት ነው” ተባባሉ። 22 ሮቤልም መልሶ፣ “በዚህ ልጅ ላይ ክፉ ነገር እንዳታደርጉ ብዬ አልነበረምን? እናንተ ግን አልሰማችሁኝም፤ ስለዚህም ደሙ ከእጃችን ይፈለጋል” አላቸው። 23 ዮሴፍ የሚያነጋግራቸው በአስተርጓሚ ስለሆነ የሚነጋገሩትን እንደሚሰማባቸው ዐላወቁም ነበር። 24 ከፊታቸውም ዘወር ብሎ አለቀሰ፤ ከዚያም ወደእነርሱ ትመልሶ እንደገና አነጋገራቸው፤ ስምዖንንም ከእነርሱ ለይቶ ዓይናቸው እያየ አሰረው፤ 25 ዮሴፍ ለአገልጋዮቹ በስልቻዎቻቸው እህል እንዲሞሉላቸው፤ ብሩንም በያንዳንዱ ሰው ስልቻ ውስጥ መልሰው እንዲያስቀምጡና ለጉዞአቸው ስንቅ እንዲያሲዟቸው ትእዛዝ ሰጠ። ይህም ተደረገላቸው። 26 እነርሱም እህላቸውን በአህዮቻቸው ጭነው ጉዞአቸውን ቀጠሉ። 27 በመንገድም ለአዳር ሰፍረው ሳለ፣ ከእነርሱ አንዱ ከያዘው እህል ላይ ለአህያው ለመስጠት ስልቻውን ሲፈታ፣ በስልቻው አፍ ላይ ብሩን አገኘ። 28 እርሱም ወንድሞቹን፣ “ኧረ ብሬ ተመልሶልኛል፤ ይኸው ስልቻዬ ውስጥ አገኘሁት” አላቸው። ሁሉም ልባቸው በድንጋጤ ተሞልቶ እየተንቀጠቀጡ በመተያየት፣ “እግዚአብሔር ምን ሊያመጣብን ይሆን?” አሉ። 29 በከነዓን ምድር ወዳለው ወደ አባታቸው ወደ ያዕቆብ ከደረሱ በኋላ ያጋጠማቸውን ሁሉ እንዲህ ብለው ነገሩት፤ 30 “የግብፅ አገር አስተዳዳሪ ‘አገሬን ልትሰልሉ የመጣችሁ ናችሁ’ በማለት በቁጣ ቃል ተናገረን፤ 31 እኛ ግን እንዲህ አልነው፤ “እኛ የታመንን ሰዎች እንጂ ሰላዮች አይደለንም። 32 እኛ የአንድ አባት ልጆች የሆንን ዐሥራ ሁለት ወንድማማቾች ነን፣ አንዱ የለም፣ ታናሽ ወንድማችን ግን ከአባታችን ጋር በከነዓን ይገኛል።’ 33 ከዚህ በኋላ የአገሩ ጌታ የሆነው ሰው እንዲህ አለን፣ “ታማኝ ሰዎች መሆናችሁን የማውቀው በዚህ ነው ከእናንተ መካከል አንዱን ወንድማችሁን እዚህ እኔ ዘንድ ትታችሁ የተቀራችሁት ለትራቡት ቤተ ሰቦቻችሁ እህል ይዛችሁላቸው ሂዱ። 34 ነገር ግን ታናሽ ወንድማችሁን ወደ እኔ አምጡት። በዚያን ጊዜም ታማኝ ሰዎች እንጂ ሰላዮች አለመሆናችሁን ዐውቃለሁ፤ ወንድማችሁንም መልሼ እሰጣችኋለሁ፤ እናንተም በምድሪቱ እንደፈለጋችሁ እየተዘዋወራችሁ መነገድ ትችላላችሁ። 35 እህሉንም ሲዘረግፉ በየስልቻቸው ውስጥ ብራቸው እንደተቋጠረ ተገኘ፤ የእያንዳንዳቸውን የተቋጠረ ብር ሲያዩም፣ እነርሱም ሆኑ አባታቸው ደነገጡ። 36 አባታቸው ያዕቆብም፣ “ያለ ልጅ እኮ አስቀራችሁኝ፣ ዮሴፍ የለም፣ ስምዖንም የለም፤ አሁን ደግሞ ብንያምን ልትወስዱ ትፈልጋላችሁ፤ በዚህ ሁሉ መከራ የምሠቃየው እኔ ነኝ” አለ። 37 በዚህን ጊዜ ሮቤል አባቱን፣ “ብንያምን ወደ አንተ መልሼ ባላመጣው ሁለቱን ወንዶች ልጆቼን ወስደህ ግደላቸው፣ ስለዚህ በእኔ ኃላፊነት ላከው፤ እኔም መልሼ አመጣዋለሁ” እለው። 38 ያዕቆብም “ምንም ቢሆን ከእናንተ ጋር አይሄድም፤ ወንድሙ ሞቶአል፣ የቀረው እርሱ ብቻ ነው፤ በመንገድ አንድ ጉዳት ቢደርስበት በእርጅናዬ ዘመን በመሪር ሐዘን ወደ መቃብር እንድወርድ ታደርጉኛላችሁ” አላቸው።