41

1 ድፍን ሁለት ዓመት ካለፈ በኋላ ፈርዖን ሕልም ዐለም፤ ሕልሙም በዓባይ ወንዝ ዳር ቆሞ ነበር፤ 2 እነሆ፣ መልካቸው ያማረ፣ ሥጋቸው የወፈረ ሰባት ላሞች ከወንዙ ወጥተው በወንዙ ዳር የበቀለውን ሣር ይበሉ ጀመር። 3 ቀጥሎም መልካቸው የከፋ አጥንታቸው የወጣ ሌሎች ሰባት ላሞች ከወንዙ ወጥተው አስቀድመው ከወጡት ላሞች አጠገብ ቆሙ። 4 እነዚህ መልካቸው የከፋና አጥንታቸው የወጣ ላሞች፥ እነዚያን ያማሩና የወፈሩ ላሞች ሲውጡአቸው ዐየ፤ ከዚያም ፈርዖን ከእንቅልፉ ነቃ። 5 ፈርዖንም እንደገና እንቅልፍ ወስዶት ሳለ ሌላ ሕልም ዐየ። በሕልሙም በአንድ የእህል አገዳ ላይ ሰባት የዳበሩና ያማሩ የእሸት ዛላዎች ዐየ፤ 6 ቀጥሎም የቀጨጩና ከበረሐ በተነሣ የምሥራቅ ነፋስ ተመትተው የደረቁ ሰባት የእሸት ዛላዎች ወጡ። 7 የቀጨጩት የእሸት ዛላዎች፤ ሰባቱን የዳበሩና ያማሩ የእሸት ዛላዎች ዋጡአቸው፤ በዚህ ጊዜ ፈርዖን ከእንቅልፉ ነቃ፣ ነገሩ ሕልም ነበር። 8 በነጋታውም ፈርዖን መንፈሱ ታወከበት፣ ስለዚህ በግብፅ አገር ያሉትን አስማተኞችና ጥበበኞች በሙሉ አስጠርቶ ሕልሞቹን ነገራቸው፣ ይሁን እንጂ፣ ሕልሞቹን ሊተረጉምለት የቻለ አንድም ሰው አልተገኘም። 9 በዚያን ጊዜ የመጠጥ አሳላፊዎቹ አለቃ ፈርዖንን እንዲህ አለው፤ “የሠራሁት በደል ዛሬ ታወሰኝ። 10 ፈርዖን ሆይ! አንተ በእኔና በእንጀራ ቤት ኃላፊው ላይ ተቆጥተህ በዘበኞች አለቃ ቤት እንድንታሰር አድርገህ ነበር፤ 11 በዚያ ሳለን በአንድ ሌሊት ሁለታችንም የተለያየ ሕልም ዐየን፤ የእያንዳንዳችንም ሕልም የተለያየ ትርጉም ነበረው። 12 በዚያን ጊዜ የዘበኞች አለቃ አገልጋይ የሆን አንድ ዕብራዊ ወጣት ከእኛ ጋር እስር ቤት ነበር። ሕልማችንን በነገርነው ጊዜ፣ ፍቺውን ነገረን፤ ለእያንዳንዳችንም እንደ ሕልማችን ተረጎመልን፤ 13 ነገሩም ልክ እርሱ እንደተረጎመልን፤ እኔ ወደ ቀድሞ ሹመቴ ተመለስሁ፤ የእንጀራ ቤት አዛዡም ተሰቀለ። 14 ፈርዖን ዮሴፍን እንዲያመጡት ትዕዛዝ ሰጠ፤ ከእስር ቤትም በጥድፊያ ይዘውት መጡ፤ ጠጉሩንም ከተላጨና ልብሱን ከለወጠ በኋላ ፈርዖን ፊት ቀረበ 15 ፈርዖንም ዮሴፍን፣ “ሕልም ዐይቼ ነበር፣ ሕልሜን ሊተረጉምልኝ የቻለ አንድም ሰው አልተገኘም፣ አንተ ግን ሕልም ሲነገርህ የመተርጎም ችሎታ እንዳለህ ሰማሁ” አለው። 16 ዮሴፍም ለፈርዖን እንዲህ ብሎ መለሰ፦ “ይህ በእኔ አይደለም፤ እግዚአብሔር ግን ለፈርዖን በበጎነት ይመልስለታል” 17 ፈርዖን ዮሴፍን እንዲህ አለው፤ “ሕልሜ በዓባይ ወንዝ ዳር ቆሜ ነበር። 18 ሥጋቸው የወፈረና መልካቸው የማረ ሰባት ላሞች ከወንዙ ወጥተው በወንዙ ዳር የበቀለውን ሣር ሲበሉ ዐየሁ። 19 ከእነርሱም በኋላ ዐቅመ ደካማ፣ መልካቸው እጅግ የከፋና አጥንታቸው የወጣ ሌሎች ሰባት ላሞች ወጡ፤ እነዚያን የመሰሉ የሚያስከፋ መልክ ያላቸው ላሞች በግብፅ ምድር ከቶ ዐይቼ አላውቅም። 20 አጥንታቸው የወጣና አስከፊ መልክ ያላቸው ላሞች መጀመሪያ የወጡትን፣ ሥጋቸው የወፈረውን ሰባቱን ላሞች ዋጧቸው። 21 ከዋጧቸውም በኋላ፣ ያው የበፊቱ መልካቸው ስላልተለወጠ እንደዋጧቸው ማንም ሊያውቅ አይችልም ነበር፤ ከዚያም ከእንቅልፌ ነቃሁ 22 ደግሞም በአንድ የእህል አገዳ ላይ ሰባት የዳበሩና ያማሩ የእሸት ዛላዎች ዐየሁ፤ 23 ቀጥሎም የቀጨጩና የደረቁ ሌሎች ሰባት ዛላዎች ወጡ። 24 የቀጨጩት የእሸት ዛላዎችም ሰባቱን ያማሩ የእሸት ዛላዎች ዋጧቸው፤ ያየኋቸውንም ሕልሞች ለአስማተኞች ነገርሁ፣ ነገር ግን ሕልሞቹን ማንም ሊተረጉምልኝ አልቻለም።” 25 ዮሴፍም ለፈርዖን እንዲህ አለው፤ “ሁለቱም የፈርዖን ሕልሞች ተመሳሳይና አንድ ዓይነት ናቸው፤ እግዚአብሔር ወደፊት የሚያደርገውን ለፈርዖን ገልጦለታል። 26 ሰባቱ የሚያምሩ ላሞች ሰባት ዓመታት ናቸው፣ ሰባቱም የሚያማምሩ የእሸት ዛላዎች ሰባት ዓመታት ናቸው፤ ሕልሙም አንድና ተመሳሳይ ነው። 27 ከእነርሱም በኋላ አጥንታቸው የወጣ አስከፊ መልክ ያላቸው ሰባት ላሞች፣ ሰባት ዓመታት ናቸው፤ እንደዚሁም ፍሬ አልባ የሆኑትና በምሥራቅ ነፋስ ተመትተው የደረቁት ሰባት የእሸት ዛላዎች ሰባት የራብ ዓመታት ናቸው። 28 አስቀድሜ ለፈርዖን እንደተናገርሁት እግዚአብሔር ወደፊት የሚያደርገውን ነገር ለፈርዖን ገልጦለታል። 29 በመላው የግብፅ ምድር እጅግ የተትረፈረፈ ጥጋብ የሚሆንባቸው ሰባት ዓመታት ይመጣሉ። 30 በዚህ በኋላ ግን በተከታታይ ሰባት የራብ ዓመታት ይሆናሉ። የራቡ ዘመን አገሪቱን እጅግ ስለሚጎዳት በግብፅ የነበረው ያለፈው የጥጋብ ዘመን ሁሉ ጨርሶ አይታወስም። 31 ከጥጋብ ዓመታት በኋላ የሚመጣው የራብ ዘመን እጅግ ጽኑ ከመሆኑ የተነሣ፣ ቀደም ሲል የነበረው የጥጋብ ዘመን ፈጽሞ ይረሳል። 32 ሕልሙ ለፈርዖን በድጋሚ መታየቱ፣ ነገሩ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተቆረጠ ስለሆነ ነው፤ ይህንንም እግዚአብሔር በቅርብ ጊዜ ይፈጽመዋል፤ 33 እንግዲህ ፈርዖን ብልኅና አስተዋይ ሰው ፈልጎ፣ በመላው የግብፅ ምድር ላይ አሁኑኑ ይሹም። 34 እንደዚሁም በሰባቱ የጥጋብ ዓመታት ከሚገኘው ምርት፣ አንድ አምስተኛው እንዲሰበሰብ የሚያደርጉ ኃላፊዎችን ይሹም። 35 እነርሱም በሚመጡት የጥጋብ ዓመታት ከሚገኘው ምርት ሁሉ ይሰብስቡ፤ በፈርዖንም ሥልጣን ሥር ያከማቹ፤ ለምግብ እንዲሆኑም በየከተማው ይጠበቁ። 36 የሚከማቸው እህል፣ ወደፊት በግብፅ አገር ላይ ለሚመጣው የሰባት ዓመት ራብ መጠባበቂያ ይሁን፤ በዚህም ሁኔታ አገሪቱ በራብ አትጠፋም። 37 ዕቅዱም ፈርዖንና ሹማምንቱ ሁሉ መልካም ሆኖ አገኙት። 38 ፈርዖንም፣ “የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት እንደዚህ ያለ ሰው ልናገኝ እንችላለን?” ብሎ ጠየቃቸው። 39 ፈርዖን ዮሴፍን እንዲህ አለው፣ “እግዚአብሔር ይህን ሁል ገለጠለህ እንዳንተ ያለ አስተዋይና ብልህ ሰው የለም። 40 አንተ በቤተ መንግሥቴ የበላይ ትሆናለህ፤ ሕዝቤም ሁሉ ለሥልጣንህ ይገዛል፤ እኔ ከአንተ የምበልጠው በዙፋኔ ብቻ ይሆናል።” 41 ከዚያም፣ ፈርዖን ዮሴፍን፣ “በመላይቱ የግብፅ ምድር ላይ ኃላፊ አድርጌሃለሁ” አለው። 42 ፈርዖንም ባለማኅተሙን ቀለበት ከጣቱ አውልቆ በዮሴፍ ጣት ላይ አደረገው፤ እንዲሁም ከጥሩ የተልባ እግር የተሠራ ልብስ አለበሰው፤ በአንገቱም የወርቅ ሐብል አጠለቀለት። 43 በማዕረግ ከእርሱ ሁለተኛ ሰው አድርጎ በሠረገላ ላይ አስቀመጠው። ሰዎችም በፊቱ፣ “እጅ ንሡ” እያሉ ይጮኹ ነበር፤ በዚህ ሁኔታም በግብፅ ምድር ሁሉ ላይ ሾመው። 44 ከዝህ በኋላ ፈርዖን ዮሴፍን፣ “እኔ ፈርዖን ነኝ፤ ሆኖም በመላይቱ ግብፅ ያለ አንተ ፈቃድ ማንም ሰው እጁን ወይም እግሩን ማንቀሳቀስ አይችልም” አለው። 45 ፈርዖን ዮሴፍን ጸፍናት ፐዕናህ ብሎ ስም አወጣለት። እንዲሁም አስናት ተብላ የምትጠራውን ኦን ተብሎ የሚጠራው ከተማ ካህን የጶጢፌራን ልጅ በሚስትነት ሰጠው። 46 ዮሴፍ የግብፅ ንጉሥ ፈርዖንን ማገልገል ሲጀምር፣ ዕድሜው ሠላሳ ዓመት ነበር። ዮሴፍም ከፈርዖን ፊት ወጥቶ የግብፅን ምድር በሙሉ ዞረ። 47 በሰባቱም የጥጋብ ዓመታት ምድሪቱ የተትረፈረፈ ሰብል ሰጠች። 48 በእነዚያ ሰባት የጥጋብ ዓመታት፣ ዮሴፍ በግብፅ አገር የተገኘውን ምርት ሰብስቦ በየከተሞቹ አከማቸ፣ በእያንዳንዱ ከተማ ከየአቅራቢያው የተመረተውን እህል እንዲከማች አደረገ። 49 ዮሴፍ ብዛቱ እንደ ባሕር አሸዋ የሚሆን የእህል ሰብል አከማቸ፤ ሰብሉ እጅግ ከመብዛቱ የተነሣ ልኩን መስፈርና መመዝገብ አልቻለም ነበር። 50 ሰባቱ የራብ ዓመታት ከመምጣታቸው በፊት የኦን ከተማ ካህን የጶጢፌራ ልጅ አስናት ለዮሴፍ ሁለት ወንድ ልጆች ወለደችለት። 51 ዮሴፍም፣ “እግዚአብሔር መከራዬን ሁሉ የአባቴንም ቤት እንድረሳ አድርጎኛል” በማለት የመጀመሪያ ልጁን ስም ምናሴ አለው። 52 እንደዚሁም “መከራ በተቀበልሁበት ምድር እግዚአብሔር ፍሬያማ አደረገኝ” ሲል ሁለተኛ ልጁን ኤፍሬም አለው። 53 በግብፅ ምድር የነበረው ሰባቱ የጥጋብ ዘመን አለፈና 54 ዮሴፍ አስቀድሞ እንደተናገረው የሰባቱ ዓመት የራብ ዘመን ጀመረ። ሌሎች አገሮች ሁሉ ሲራቡ፣ በመላው የግብፅ ምድር መስፋፋት ሲጀመር፣ 55 ሕዝቡ ምግብ ይሰጠን በማለት ወደ ፈርዖን ጮኸ። ፍርዖንም ግብፃውያኑን፣ “ወደ ዮሴፍ ሂዱና የሚላችሁን አድርጉ” አላቸው። 56 ራቡ በአገሩ ላይ እየተስፋፋ ስለሄደ፣ ዮሴፍ ጎተራዎቹን ከፍቶ እህሉ ለግብፃውያን እንዲሸጥ አደረገ፤ ምክንያቱም ራቡ በመላይቱ ግብፅ ጸንቶ ነበር። 57 ራቡ በመላው ዓለም ጸንቶ ስለነበር፣ የየአገሩ ሰዎች ሁሉ ከዮሴፍ ዘንድ እህል ለመሸመት ወደ ግብፅ ምድር መጡ።