40

1 ከዚህም በኋላ የግብፅ ንጉሥ የመጠጥ አሳላፊውና የእንጀራ ቤት ኃላፊው ንጉሡን የሚያሳዝን በደል ፈጸሙ። 2 ፈርዖንም በመጠጥ አሳላፊዎቹ አለቃና በእንጀራ ቤቱ አዛዡ፣ በሁለቱም ሹማምንቱ ላይ እጅግ ተቆጣ፤ 3 በዘበኞቹ አለቃ ቤት ወዳለው ዮሴፍ ወደታሠረበት እስር ቤት አስገባቸው። 4 የዘበኞቹም አለቃ እስረኞቹን ለዮሴፍ አስረከባቸው፤ በእስር ቤትም ለጥቂት ጊዜ ቆዩ። 5 ታስረው የነበሩት የግብፅ ንጉሥ የመጠጥ አሳላፊዎች አለቃና የእንጀራ ቤቱ አዛዥ፣ በአንድ ሌሊት የየራሳቸውን ሕልም ዐዩ፤ የሁለቱም ሕልም ለየራሱ የተለየ ፍቺ ነበረው። 6 በማግስቱ ጥዋት ዮሴፍ እነርሱ ወዳሉበት ክፍል በገባ ጊዜ ተክዘው አገኛቸውና፤ 7 “ዛሬ በፊታችሁ ላይ ሐዘን የሚታየው ለምንድን ነው?” አላቸው። 8 እነርሱም፣ “ሁለታችንም ሕልም ዐየን፤ ነገር ግን የሚተረጉምልን ሰው አጣን” ሲሉ መለሱለት። ዮሴፍም፣ “ሕልም የመተርጎም ችሎታ የሚሰጥ እግዝአብሔር ነው፣ ስለዚህ የእያንዳንዳችሁን ሕልም ንገሩኝ” አላቸው። 9 ስለዚህ የመጠጥ አሳላፊዎቹ አለቃ እንዲህ ሲል ሕልሙን ለዮሴፍ ነገረው፤ “ከፊት ለፊቴ አንዲት የወይን ተክል ዐየሁ፤ 10 ተክሏም ሦስት ሐረጎች ነበሯት፤ ወዲያው እቆጥቁጣ አበበች፤ የወይን ዘለላውም ወዲያው በሰለ። 11 የፈርዖንንም ጽዋ ይዤ ነበር፣ የወይኑን ፍሬ ለቅሜ በጽዋው ውስጥ ጨምቄ ጽዋውን በእጁ ሰጠሁት።” 12 ዮሴፍም እንዲህ አለው፤ “እንግዲህ የሕልሙ ትርጓሜ ይህ ነው፤ ሦስቱ ሐረግ ሦስት ቀን ነው፤ 13 በሦስት ቀን ውስጥ ፈርዖን ከእስር ቤት ያወጣሃል፣ ወደ ቀድሞ ሹመትህም ይመልስሃል፤ በፊት የመጠጥ አሳላፊ በነበርህበት ጊዜ ታደርግ እንደነበረው ኡሉ የፈርዖንን ጽዋ በእጁ ትሰጠዋለህ። 14 እንግዲህ፣ በጎ ነገር በገጠመህ ጊዜ፣ እኔን አስበህ ቸርነት አድርግልኝ፣ ስለ እኔም ለፈርዖን ንገርልኝ፤ ከዚህም እስር ቤት አስወጣኝ፤ 15 ከዕብራውያን ምድር ወደዚህ የመጣሁት በአፈና ነው፤ አሁንም ቢሆን እዚህ እስር ቤት የተጣልሁት አንዳች ጥፋት ኖሮብኝ አይደለም።” 16 የእንጀራ ቤት አዛዡም፣ ለመጠጥ አሳላፊዎቹ አለቃ ሕልም የተሰጠው ፍቺ ደስ የሚያሰኝ መሆኑን ሲሰማ፣ የራሱን ሕልም ለዮሴፍ እንዲህ ሲል ነገረው፤ “እኔም ደግሞ ሕልም አይቻለሁ፣ ሦስት መሶቦች በራሴ ላይ ተሸክሜ ነበር፤ 17 በላይኛው መሶብ ውስጥ ለፈርዖን የተዘጋጀ የተለያየ ምግብ ነበረበት፣ ነገር ግን ወፎች ምግቡን ከመሶቡ እያነሱ የበሉት ነበር።” 18 ዮሴፍም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “የሕልሙ ፍቺ ይህ ነው፤ ሦስቱ መሶብ ሦስት ቀን ነው፤ 19 በሦስት ቀን ውስጥ ፈርዖን ራስህን ካስቆረጠ በኋላ በእንጨት ላይ ይሰቅልሃል፤ ወፎችም ሥጋህን የበሉታል።” 20 በሦስተኛው ቀን የፈርዖን ልደት በዓል ስለነበር ለመኳንንቱ ሁሉ ግብዣ አደረገ፤ በዚያኑ ዕለትም የመጠጥ አሳላፊዎቹን አለቃና የእንጀራ ቤት አዛዡን ሹማምንቱ ካሉበት ከእስር ቤት አወጣቸው። 21 የመጠጥ አሳላፊዎቹን አለቃ ወደ ቀድሞ ሹመቱ መለሰው፤ እርሱም እንደ ቀድሞው ጽዋውን ለፈርዖን በእጁ ይሰጠው ጀመር፤ 22 የእንጀራ ቤት አዛዡን ግን ልክ ዮሴፍ እንደተረጎመላቸው ሰቀለው። 23 የሆነው ሆኖ፣ የመጠጥ አሳላፊዎቹ አለቃ ዮሴፍን አላስታወሰውም፤ ረሳው።