45

1 በዚያን ጊዜ ዮሴፍ አጠገቡ በነበሩ ሰዎች ፊት ስሜቱን ሊገታ ባለመቻሉ፣ “እዚህ ያሉትን ሰዎች በሙሉ አስወጡልኝ” ብሎ ጮኾ ተናገረ፤ ስለዚህም ዮሴፍ ራሱን ለወንድሞቹ በገለጠበት ጊዜ ከእርሱ ጋር ሌላ ማንም ሰው አልነበረም። 2 ዮሴፍም ድምፁን ከፍ አድርጎ በማልቀሱ ግብፃውያን ሰሙት፣ ወሬውም ወደ ፈርዖን ቤተ ሰዎች ደረሰ። 3 ዮሴፍም ወንድሞቹን፣ “እኔ ዮሴፍ ነኝ፤ ለመሆኑ አባቴ እስካሁን በሕይወት አለ?” ሲል ጠየቃቸው። ወንድሞቹ ግን በፊቱ ተደናግጠው ስለነበር መልስ ሊሰጡት አልቻሉም። 4 ዮሴፍም ወንድሞቹን፣ “እስቲ ወደ እኔ ቀረብ በሉ” አላቸው፣ ወደ እርሱም በቀረቡ ጊዜ እንዲህ አለ፤ “ወደ ግብፅ የሸጣችሁኝ እኔ ዮሴፍ ነኝ፤ 5 አሁንም በመሸጣችሁ አትቆጩ፤ በራሳችሁም አትዘኑ፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር ሕይወት ለማዳን ሲል ከእናንተ አስቀድሞ እኔን ወደዚህ ልኮኛል። 6 በምድር ላይ ራብ ከገባ ይኸው ሁለት ዓመት ሆነ፣ ከዚህ በኋላም የማይታረስባቸውና ሰብል የማይሰበሰብባቸው አምስት ዓመታት ገና አሉ። 7 ነገር ግን እግዚአብሔር ሕይወታችሁን በታላቅ ማዳን ለመታደግና ዘራችሁ ከምድር ላይ እንዳይጠፋ በማሰብ ከእናንተ አስቀድሞ ወደዚህ ላከኝ። 8 ስለዚህ አሁን ወደዚህ የላከኝ እግዚአብሔር እንጂ እናንተ አይደላችሁም፣ እርሱም ለፈርዖን እንደ አባት፤ በቤት ንብረቱ ላይ ጌታ፣ እንዲሁም በግብፅ ምድር ላይ ገዢ አደረገኝ። 9 አሁንም ‘በፍጥነት ወደ አባቴ ተመልሳችሁ እንዲህ በሉት፤ “ልጅህ ዮሴፍ እንዲህ ይላል፤ ‘እግዚአብሔር የመላው ግብፅ ጌታ አድርጎኛል፤ ስለዚህ ሳትዘገይ ወደ እኔ ና። 10 ልጆችህን የልጅ ልጆችህን በጎችህን፣ ፍየሎችህን ከብቶችህንና ያለህን ሁሉ ይዘህ በአቅራቢያዬ በጌሤም ትኖራለህ። 11 ገና ወደ ፊት የሚመጣ የአምስት ዓመት ራብ ስላለ፣ በዚያ የሚያስፈልጋችሁን እኔ እሰጣችኋለሁ፤ ያለበልዚያ ግን አንተና ቤተ ስዎችህ ያንተም የሆነው ሁሉ፣ ችግር ላይ ትወድቃላችሁ።’ 12 ፊታችሁ ሆኜ የማናግራችሁ እኔ ዮሴፍ ራሴ መሆኔን እናንተም ሆናችሁ ወንድሜ ብንያም በዓይናችሁ የምታዩት ነው። 13 በግብፅ ስላሏኝ ክብርና ስላያችሁትም ሁሉ ለአባቴ ንገሩት፣ አባቴንም በፍጥነት ይዛችሁት ኑ። 14 ከዚያም በወንድሙ በብንያም አንገት ላይ ተጠምጥሞ አለቀሰ፤ ብንያምም እያለቀሰ ዮሴፍን አቀፈው። 15 የቀሩትምንም ወንድሞቹን አንድ በአንድ እየሳመ አለቀሰ። ከዚያም ወንድሞቹ ከእርሱ ጋር መጨዋወት ጀመሩ። 16 የዮሴፍ ወንድሞች መምጣት በፈርዖን ቤተ መንግሥት በተሰማ ጊዜ፣ ፈርዖንና ሹማምንቱ ሁሉ ደስ አላቸው። 17 ፈርዖን ዮሴፍን እንዲህ አለው፤ “ለወድሞችህ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፣ ‘እንዲህ አድርጉ እህዮቻችሁን ጭናችሁ ወደ ከነዓን ምድር ተመለሱ። 18 ከዚያም አባታችሁንና ቤተ ሰባችሁን ይዛችሁ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም እጅግ ለም ከሆነው የግብፅ ምድር እሰጣችኋለሁ፤ በምድሪቱ በረከት ደስ ብሎአችሁ ትኖራላችሁ።’ 19 ደግሞም እንዲህ ብለህ እዘዛቸው፤ ‘ይህን አድርጉ፣ ከግብፅ ምድር ልጆቻችሁንና ሚስቶቻችሁን የምታጓጉዙባቸው ሠረገላዎች ወስዳችሁ፤ አባታችሁን ይዛችሁ ኑ። 20 ስለ ንብረታችሁ ምንም አታስቡ፣ ከግብፅ ምድር እጅግ ለም የሆነው የእናንተ ይሆናልና።’” 21 የእስራኤልም ልጆች ይህንኑ አደረጉ። ዮሴፍም ፈርዖን ባዘዘው መሠረት ሠረገላዎች አቀረበላቸው፤ የመንገድም ስንቅ አስያዛቸው። 22 ለእያንዳንዳቸው ሁለት ሁለት የክት ልብስ ሰጣቸው፤ ለብንያም ግን ሶስት መቶ ጥሬ ብርና አምስት የክት ልብስ ሰጠው። 23 ለአባቱም በግብፅ ምድር ከሚገኘው የተመረጠ ነገር በዐሥር አህዮች፣ እንደዚሁም በዐሥር እንስት አህዮች ዳቦና ሌላ ምግብ አስጭኖ ሰደደለት። 24 ከዚህ በኋላ ወንድሞቹን አሰናበታቸው፤ ከእርሱም ሲሰናበቱ፣ መንገድ ላይ እንዳትጣሉ” አላቸው። 25 እነርሱም ከግብፅ ወጥረው በከነዓን ምድር ወደሚኖረው ወደ አባታቸው ወደ ያዕቆብ መጡ። 26 አባታቸውንም፣ እነሆ ዮሴፍ በሕይወት አለ፤ እንዲያውም በግብፅ ምድር ሁሉ ገዥ ሆኖአል” ብለው ነገሩት። ያዕቆብ ግን እጅግ ደነገጠ፤ ሊያምናቸውም አልቻለም። 27 ነገር ግን ዮሴፍ ያላቸውን ሁሉ በነገሩት ጊዜና እርሱን ወደ ግብፅ የሚወስዱበትን ዮሴፍ የላከለትን ሠረገላ ባየ ጊዜ የአባታቸው የያዕቆብ መንፈስ ታደሰ። 28 ከዚያም እስራኤል፣ “ልጄ ዮሴፍ በሕይወት አለ፤ ከመሞቴ በፊት ሄጄ ዐየዋለሁ” አለ።