32

1 ያዕቆብ በጉዞ ላይ ሳለ የእግዚአብሔር መላእክት በመንገድ ተገናኙት። 2 ባያቸውም ጊዜ፤ “ይህ የእግዚአብሔር ሰፈር ነው” አለ፤ የዚያንም ቦት ስም መሃናይም አለው። 3 ያዕቆብም በኤዶም አገር ሴይር በተባለው ምድር ወደሚኖረው ወንድሙ ወደ ዔሳው መልእክተኞችን አስቀድሞ ላከ፤ 4 እንዲህም ብሎ አዘዛቸው፤ “ጌታዬን ዔሳውን እንዲህ ትሉታላችሁ፤ ‘አገልጋይህ ያዕቆብ እንዲህ ብሎአል በሉት፤ ከላባ ዘንድ ተቀምጬ እስካሁን ድረስ እዚያው ኖርሁ፤ 5 ከብቶች፣ አህዮች፣ የበግና የፍየል መንጎች እንደዚሁም የወንድን የሴት አገልጋዮች አሉኝ፤ አሁንም ይህን መልእክት ለጌታዬ መላኬ በአንተ ዘንድ ሞግስ አገኛለሁ በሚል ተስፋ ነው።’” 6 የተላኩትም ሰዎች ወደ ያዕቆብ ተመልሰው፣ “ወደ ወንድምህ ወደ ዔሳው ሄደን ነበር፤ እርሱም ከአንት ጋር ለመገናኘት በመምጣት ላይ ነው፤ ከእርሱም ጋር አራት መቶ ሰዎች አሉ” አሉት። 7 በዚህ ጊዜ ያዕቆብ እጅግ በመፍራት ተጨነቀ፤ አብረውት የነበሩትንም ሰዎች በሁለት ክፍል መደባቸው፤ እንዲሁም በጎቹን፣ ፍየሎቹን፣ ከብቶቹንና ግመሎቹን በሁለት በሁለት መደባቸው። 8 ይህንንም ያደረገው፦ “ዔሳው የመጀመሪያውን ክፍል ቢያጠቃ፣ ሌላው ክፍል ሊያመልጥ ይችላል” ብሎ በማሰብ ነው። 9 ያዕቆብ እንዲህ ሲል ጸለየ፤ “የአባቴ የአብርሃም አምላክ፣ የአባቴ የይስሐቅ አምላክ ሆይ፣ ‘ወደ አገርህና ወደ ዘመዶችህ ተመልስ፣ እኔም በጎ ነገር አደርግልሃለሁ’ ያልኸኝ እግዚአብሔር ሆይ፣ 10 እኔ ባሪይህ እስካሁን ላደረግህልኝ ቸርነትና ታማኝነት ብቁ አይደለሁም፤ ዮርዳኖስን ስሻገር በእጄ ላይ ከነበረው በትር በስተቀር ምንም አልነበረኝም፤ አሁን ግን ይኸው ሁለት ሠራዊት ሆኛለሁ። 11 ከወንድሜ ከዔሳው እጅ እንድታድነኝ እለምንሃለሁ፤ መጥቶ እኔንም ሆነ እነዚህን እናቶች ከነልጆቻቸው ያጠፋናል ብዬ ፈርቻለሁኝ፤ 12 ነገር ግን አንተ ራስህ፣ ‘አበለጽግሃለሁ፤ ዘርህንም ሊቆጠር እንደማይችል እንደ ባሕር አሸዋ አበዛዋለሁ’ ብለኸኛል።” 13 በዚያችም ሌሊት ያዕቆብ እዚያው አደረ፤ ካለው ሀብት ለወንድሙ ለኤሳው እጅ መንሻ እንዲሆኑ እነዚህን መረጠ፦ 14 ሁለት መቶ እንስት ፍየሎችና ሃያ አውራ ፍየሎች፣ ሁለት መቶ እንስት በጎችና ሃያ አውራ በጎች፣ 15 ሠላሳ የሚያጠቡ ግመሎች ከነግልገሎቻቸው፣ አርባ ላሞችና ዐሥር ኮርማዎች፣ ሃያ እንስት አህዮችና ዐሥር ተባት አህዮች። 16 እነዚህንም በየመንጋው ለይቶ፣ የሚነዱአቸውን ጠባቂዎች መደበላቸው፤ ጠባቂዎችንም እናንተ ቀድማችሁ ሂዱ፣ መንጋዎቹንም አራርቃችሁ ንዱአቸው” አላቸው። 17 ቀድሞ የሚሄደውንም እንዲህ ሲል አዘዘው፤ ዔሳው አግኝቶህ ‘የማን ነህ? ወዴትስ ትሄዳለህ? የምትነዳውስ ይህ ሁሉ ከብት የማን ነው?’ ብሎ ቢጠይቅህ፣ 18 ‘የአገልጋይህ የያዕቆብ ናቸው፤ ለጌታዬ ለዔሳው እጅ መንሻ የሰደዳቸው ናቸው፤ እርሱም ከበስተኋላችን እየመጣ ነው’ ብለህ ንገረው 19 እንዲሁም ሁለተኛውን፣ ሦስተኛውንና መንጎቹን የሚነዱትን ሌሎቹንም ሁሉ እንዲህ ሲል አዘዛቸው፤ ‘ዔሳውን ስታገኙት ይህንኑ ትነግሩታላችሁ፤ 20 በተጨማሪም ‘አገልጋይህ ያዕቆብ ከኋላችን እየመጣ ነው’ በሉት። ይህንንም ያዘዘው፣ ‘ዔሳው ከእኔ ጋር ከመገናኘቱ በፊት እጅ መንሻዬ አስቀድሞ ቢደርሰው ምናልባት ልቡ ይራራና በሰላም ይቀበለኛል’ ብሎ ስላሰበ ነበር። 21 ስለዚህ የያዕቆብ እጅ መንሻ ከእርሱ አስቀድሞ ተላከ፤ እርሱ ራሱ ግን እዚያው በሰፈሩ ቦታ አደረ። 22 በዚያኑ ሌሊት ያዕቆብ ተነሣ ሁለቱን ሚስቶቹን፣ ሁለቱን ሴት አገልጋዮቹንና ዐሥራ አንዱን ልጆቹን ይዞ የያቦቅን ወንዝ ተሻገረ። 23 ወንዙን አሻግሮ ከሸኛቸው በኋላ፣ ጓዙን ሁሉ ሰደደ። 24 ያዕቆብም ብቻውን እዚያ ቀረ፤ አንድ ሰውም እስኪነጋ ድረስ ሲታገለው አደረ። 25 ያም ሰው ያዕቆብን ታግሎ ማሸነፍ እንዳቃተው በተረዳ ጊዜ፣ የጭኑን ሹልዳ መታው፣ ያዕቆብም በሚታገልበት ጊዜ ጭኑ ከመገጣጠሚያው ላይ ተለያየ፤ 26 በዚያን ጊዜ ሰውዬው፣ “እንግዲህ መንጋቱ ስለሆን ልቀቀኝና ልሂድ” አለው። ያዕቆብም፣ “ካልባረክኸኝ አልለቅህም” አለው። 27 ሰውዬውም፣ “ስምህ ማን ነው?” አለው። እርሱም፣ “ያዕቆብ ነው” አለ። 28 ሰውዬውም፣ “ከእግዚአብሔርም ከሰዎችም ጋር ታግለህ አሸንፈሃልና ከእንግዲህ ስምህ እስራኤል እንጂ ያዕቆብ አይባልም” አለው። 29 ያዕቆብም፣ “እባክህ ስምህን ንገረኝ” ብሎ ጠየቀው። ሰውዬውም፣ “ስሜን ለማወቅ ለምን ፈለግህ?” አለው፤ በዚያም ስፍራ ባረከው። 30 ስለዚህ ያዕቆብ “እግዚአብሔርን ፊት ለፊት ዐይቼ እንኳ ሕይወቴ ተርፋለች” ሲል የዚያን ቦታ ስም ጵኒኤል አለው። 31 ጵኒኤልንም እንዳለፈ ፀሐይ ወጣችበት፣ እርሱም በጭኑ ምክንያት ያነክስ ነበር። 32 ከዚህም የተነሣ የእስራኤል ልጆች ሹልዳን ከጭኑ ጋር የሚያገናኘውን ሥጋ አይበሉም፤ ምክንያቱም ያዕቆብ ከሰውዬው ጋር ሲታገል ሰውዬው ሹልዳውን መትቶት ስለነበር ነው።