33

1 ያዕቆብ አሻግሮ ተመለከተ፤ እነሆ፣ ዔሳው አራት መቶ ሰዎች አስከትሎ እየመጣ ነበር። ስለዚህ ያዕቆብ ልጆቹን ለልያ ለራሔልና ለሁለቱ አገልጋዮቹ አከፋፈላቸው። 2 ከዚያም ሁለቱን አገልጋዮች ከነልጆቻቸው አስቀደመ፤ ልያንና ልጆቿንም አስከተለ፤ ራሔልንና ዮሴፍን ግን ከሁሉ ኋላ እንዲሆኑ አደረገ። 3 እርሱ ራሱም ቀድሞአቸው ሄደ፤ ወንድሙም ዘንድ እስኪደርስ ድረስ ሰባት ጊዜ ወደ መሬት ለጥ ብሎ እጅ ነሣ። 4 ዔሳው ግን ሊገናኘው ወደ እርሱ ሮጦ ሄዶ አቀፈው፤ በአንገቱም ላይ ተጠምጥሞ ሳመው፤ ሁለቱም ተላቀሱ። 5 ከዚያም ዔሳው ቀና ብሎ ሲመለከት ሴቶቹንና ልጆቹን ዐየ፤ እርሱም፣ “እነዚህ አብረውህ ያሉ እነማን ናቸው?” ብሎ ጠየቀው። ያዕቆብም መልሶ፣ “እነዚህማ እግዚአብሔር በቸርነቱ ለእኔ ለአገልጋይህ የሰጠኝ ልጆች ናቸው” አለው። 6 በዚህ ጊዜ ሁለቱ ሴት አገልጋዮችና ልጆቻቸው ቀርበው እጅ ነሡ፤ 7 ከዚያም ልያና ልጆቿ መጥተው እጅ ነሡ፤ በመጨረሻም ዮሴፍና ራሔል መጡ፤ እነርሱም ቀርበው እጅ ነሡ። 8 ዔሳውም፣ “ወደ እኔ ተነድቶ የመጣው ይህ ሁሉ መንጋ ምንድነው?” አለው። ያዕቆብም፣ “ጌታዬ ሆይ፣ በአንተ ዘንድ ሞገስ ባገኝ ብዬ ነው” አለው። 9 ዔሳው ግን፣ “ወንድሜ ሆይ፤ እኔ በቂ አለኝ፤ የራስህን ለራስህ አድርገው” አለው። 10 ያዕቆብም፣ “የለም፣ እንዲህ አይደለም፤ በአንተ ዘንድ ሞገስ አግኝቼ እንደሆነ፣ እጅ መንሻዬን ተቀበል፤ በመልካም ሁኔታ ተቀብለኸኝ ፊትህን ማየት መቻሌ ራሱ፣ የእግዚአብሔርን ፊት የማየት ያህል እቆጥረዋለሁ። 11 እግዚአብሔር በቸርነቱ አሟልቶ ስለ ሰጠኝ የሚያስፈልገኝ ሁሉ አለኝና ያቀረብሁልህን እጅ መንሻ እባክህ ተቀበለኝ” አለው። ያዕቆብ አጥብቆ ስለለመነው፣ ዔሳው እጅ መንሻውን ተቀበለ። 12 ዔሳውም፣ “እንግዲህ እንሂድ፤ እኔም ከአንተ ቀድሜ እሄዳለሁ” አለው። 13 ያዕቆብ ግን እንዲህ አለው፤ “ጌታዬ እንደምታየው ልጆቹ ይህን ያህል የጠኑ አይደሉም፣ ለሚያጠቡት በጎችና ጥገቶች እንክብካቤ ማድረግ አለብኝ፤ እንስሳቱ ለአንዲት ቀን እንኳ በጥድፊያ ቢነዱ በሙሉ ያልቃሉ። 14 ስለዚህ ጌታዬ፣ አንተ ቀድመኸኝ ሂድ፤ እኔም በምነዳቸው እንስሳትና በልጆቹ ጉዞ አቅም ልክ እያዘገምሁ ሴይር ላይ እንገናኛለን” 15 ዔሳው፣ “እንግዲያስ ከሰዎቼ ጥቂቶቹን ልተውልህ” አለው። ያዕቆብ ግን፣ “ለምን ብለህ? በአንተ ዘንድ ሞገስ ማግኘቴ ይበቃኛል” አለው። 16 ስለዚህ ዔሳው በዚሁ ዕለት ወደ ሴይር ለመመለስ ተነሣ። 17 ያዕቆብ ግን ወደ ሱኮት ሄደ፤ እዚያም ለራሱ መጠለያ፣ ለከብቶቹም በረት ሠራ፤ ከዚህም የተነሣ የቦታው ስም ሱኮት ተባለ። 18 ያዕቆብ ከመስጴጦምያ በተመለሰ ጊዜ በከነዓን ምድር ወዳለችው ወደ ሴኬም በሰላም ደረሰ፤ በከተማይቱም ፊት ለፊት ሰፈረ። 19 ድንኳኑን የተከለበትንም ቦታ የሴኬም አባት ከነበረው ከኤሞር በመቶ ጥሬ ብር ገዛው፤ 20 በዚያም መሠዊያ አቁሞ፤ ኤል ኤሎሄ እስራኤል ብሎ ጠራው።