31

1 የላባ ወንዶች ልጆች፣ “ያዕቆብ የአባታችንን ሀብት እንዳለ ወስዶታል፤ ይህ ሁሉ እርሱ ያከማቸውም ሀብት ከአባታችን የተገኘ ነው” እያሉ ሲያወሩ ያዕቆብ ሰማ። 2 በላባም ዘንድ እንደቀድሞ ተወዳጅ አለመሆኑን ተረዳ። 3 እግዚአብሔርም ያዕቆብን፣ “ወደ አባቶችህ ወደ ዘመዶችህ አገር ተመለስ፤ እኔም ከአንተ ጋር እሆናለሁ” አለው። 4 ስለዚህ ያዕቆብ መንጋዎቹ ወደ ተሰማሩበት መስክ እንዲመጡ ራሔልንና ልያን አስጠራቸው፤ 5 እንዲህም አላቸው፤ “አባታችሁ ስለ እኔ ያለው አመለካከት እንደ ቀድሞ አለመሆኑን ተረድቻለሁ፤ ቢሆንም የአባቴ አምላክ አልተለየኝም፤ 6 መቼም ባለኝ አቅም አባታችሁን ማገልገሌን እናንተ ታውቃላችሁ። 7 አባታችሁ ደመወዜን ዐሥር ጊዜ እየለዋወጠ አታልሎኛል፣ ሆኖም እንዲጎዳኝ እግዚአብሔር አልፈቀደለትም። 8 እርሱ፣ ‘ደመወዝህ ዝንጉርጉሮቹ ይሆናሉ ሲለኝ፣ መንጎቹ ሁሉ ዝንጉርጉር ወለዱ’፤ ደግሞም፣ ‘ደመወዝህ ሽመልመሌዎቹ ይሆናሉ ሲለኝ፣ መንጎቹ ሁሉ ሽመልመሌ መልክ ያላቸውን ወለዱ፤ 9 ስለዚህ እግዚአብሔር የአባታችሁን ከብቶች ወስዶ ለእኔ ሰጠኝ። 10 እንስሳቱ በሚጠቁበት ወራት የሚያጠቋቸው አውራ ፍየሎች ሽመልመሌ፣ ዝንጉርጉርና ነቁጣ መሆናቸውን በሕልም አየሁ። 11 በዚያው ሕልም የእግዚአብሔር መልአክ፦ ‘ያዕቆብ’ ብሎ ጠራኝ፣ እኔም ‘እነሆ አለሁ’ አልሁ። 12 እርሱም እንዲህ አለኝ፦ ‘መንጋዎቹን የሚያጠቋቸው አውራ ፍየሎች ሽመልመሌ፣ ዝንጉርጉርና ነቁጣ ያለባቸው መሆናቸውን ተመልከት፣ ላባ የፈጸመብህን በደል አይቻለሁ። 13 የድንጋይ ሐውልት በማቆም ዘይት ቀብተህ የተሳልህባት የቤቴል አምላክ እኔ ነኝ፤ አሁንም ይህን አገር ፈጥነህ ልቀቅ ወደ ተወለድህበትም ምድር ተመልሰህ ሂድ’ አለኝ።” 14 ራሔልና ልያም እንዲህ ብለው መለሱለት፦ “ከአባታችን የምንወርሰው ድርሻ አለን? 15 እርሱ እኛን የሚያየን እንደ ባዕዳን አይደለምን? ደግሞም እኮ እኛን ሽጦናል፣ የተሸጥንበትንም ዋጋ ራሱ በልቶታል። 16 እግዚአብሔር ከአባታችን ወስዶ ለአንተ የሰጠው ሀብት ሁሉ የእኛና የልጆቻችን ነው፤ ስለዚህ እግዚአብሔር የነገረህን ሁሉ አድርግ።” 17 ከዚያም ያዕቆብ ተነሥቶ ልጆቹንና ሚስቶቹን በግመሎች ላይ አስቀመጠ፤ 18 በመስጴጦምያ ካፈራው ሀብት ሁሉ ጋር ከብቶቹን በሙሉ ወደፊት አስቀደመ፣ ወደ አባቱም ወደ ይስሐቅ አገር፣ ወደ ከነዓን ምድር ጉዞውን ቀጠለ። 19 ላባ በጎቹን ሊሸልት ሄዶ ስለነበር፣ እርሱ በሌለበት ራሔል ከቤት የነበሩትን የአባቷን ጣዖቶች ሰርቃ ሄደች። 20 ያዕቆብ መሄዱን ለላባ ሳይገልጥለት አታሎት ሄደ፣ 21 የራሱ የሆነውን ሀብት ይዞ በፍጥነት ታጓዘ፤ የኤፍራጥስንም ወንዝ ተሻግሮ ወደ ኮረብታማው አገር ወደ ገለዓድ ሄደ። 22 ያዕቆብ መኮብለሉን ለላባ በሦስተኛው ቀን ተነገረው። 23 ከዘመዶቹ ጋር ሆኖ ያዕቆብን ተከታተለው፤ ሰባት ቀን ከተጓዙ በኋላ ገለዓድ በተባለው ተራራማ አገር ላይ ሊደርስበት ተቃረበ። 24 በዚያን ሌሊት እግዚአብሔር ለላባ በሕልም ተገለጠለትና “ያዕቆብን ክፉም ሆን ደግ እንዳትናገረው ተጠንቀቅ” አለው። 25 ያዕቆብ ገለዓድ በተባለው ኮረብታማ ስፍራ ድንኳኑን በመትከትል ሰፍሮ ሳለ ላባ ደረሰበት፤ ላባና ዘመዶቹም እዚያው ድንኳናቸውን ተክለው ሰፈሩ። 26 ከዚህ በኋላ ላባ ያዕቆብን እንዲህ አለው፦ “ስለምን እንዲህ አድርገህ አታለልኸኝ፤ ሴቶች ልጆቼንስ በጦርነት እንደተማረኩ ያህል ይዘሃቸው ለምን ሄድህ? 27 ሳትነግረኝ ተሰውረህ በመሄድ ለምን አታለልኽኝ? ነግረኸኝ ቢሆን በከበሮና በመስንቆ እየተዘፈነ በደስታ በሸኘሁህ ነበር። 28 ልጆቼንና የልጅ ልጆቼን በመሳም እንድሰናበታቸው ባለማድረግህ የሞኝነት ተግባር ፈጽመሃል። 29 ጉዳት ሳደርስብህ እችል ነበር፣ ነገር ግን ባለፈው ሌሊት የአባትህ አምላክ፣ ‘ያዕቆብን ክፉም ሆነ ደግ አንድ ቃል እንዳትናገረው’ ብሎ አስጠነቀቀኝ፣ 30 ወደ ትውልድ አገርህ ለመመለስ ባለህ ብርቱ ፍላጎት እንደተለየኸኝ አውቃለሁ፣ ታዲያ የቤቴን ጣዖቶች የሰረቅኽብኝ ለምንድነው?” 31 ለላባ እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “ሴቶች ልጆችህን በኃይል ነጥቀህ ታስቀርብኛለህ ብዬ ስለ ፈራሁ ነው በድብቅ የሄድኩት። 32 ነገር ግን ከእኛ መካከል የአንተን የጣዖት ምስል የሰረቀ ሰው ካለ ይሙት። የአንተ የሆነ አንዳች ነገር ከኔ ዘንድ ቢገኝ፣ አንተው ራስህ ዘመዶቻችን ባሉበት ፈልግና ውሰድ።” እንደዚህ ሲል ራሔል የጣዖታቱን ምስል መስረቋን ያዕቆብ አያውቅም ነበር። 33 ላባም ወደ ያዕቆብ ድንኳንና ወደ ልያ ድንኳን እንዲሁም ወደ ሁለቱ ደንገጡሮቹ ድንኳን ገባ፤ ነገር ግን ምንም አላገኘም። ከልያ ድንኳን ከወጣ በኋላ ወደ ራሔል ድንኳን ገባ። 34 ራሔል ግን ጣዖቱቹን ወስዳ በግመሉ ኮርቻ ሥር በመሰወር በላያቸው ተቀምጣባቸው ነበር። ላባ በድንኳኑ ውስጥ ያለውን ጓዝ ሁሉ በርብሮ ምንም ነገር አላገኘም። 35 ራሔልም አባቷን፦ “በፊትህ ተነሥቼ መቆም ስላልቻልሁ፣ ጌታዬ አትቆጣ የወር አበባዬ መጥቶ ነው” አለችው፤ ስለዚህ በረበረ፤ የጣዖቱን ምስል ግን ማግኘት አልቻለም። 36 በዚህ ጊዜ ያዕቆብ ተቆጣ፤ ላባንም እንዲህ ሲል ወቀሰው፦ “እስቲ ወንጀሌ ምንድን ነው? ይህን ያህል የምታሳድደኝ ኃጢአቴ ምን ቢሆን ነው? 37 ዕቃዬን አንድ በአንድ በርብረሃል፤ ታዲያ የአንተ ሆኖ ያገኘኸው ዕቃ የትኛው ነው? ካለ፣ እስቲ በአንተም በእኔም ዘመዶች ፊት አቅርብና እነርሱ ያፋርዱን። 38 ሃያ ዓመት አብሬህ ኖሬአለሁ፤ በጎችህና ፍየሎችህ አልጨነገፉም፤ ከመንጋህም አንድ ጠቦት እንኳ አልበላሁም። 39 አውሬ የሰበረውንም ቢሆን እተካ ነበር፣ በቀንም ሆነ በሌሊት የተሰረቁትን ሁሉ ስታስከፍለኝ ኖረሃል። 40 ብዙ ጊዜ በቀን ሐሩርና በሌሊት ቁር እሠቃይ ነበር፤ በቂ እንቅልፍ ያገኘሁበት ጊዜ አልነበረም። 41 ሃያ ዓመት በቤትህ የኖርሁት በዚህ ሁኔታ ነበር፤ ዐሥራ አራት ዓመት ለሁለቱ ልጆችህ ብዬ አገለገልሁ፤ ስድስት ዓመት ስለመንጋዎችህ ስል አገለገልሁ፤ ይህም ሆኖ ደመወዜን ዐሥር ጊዜ ለዋውጠኽብኛል። 42 የአባቴ አምላክና እርሱም የሚፈራው የአብርሃም አምላክ ከእኔ ጋር ባይሆን ኖሮ ባዶ እጄን ሰድደኸኝ ነበር፤ እግዚአብሔር ግን መከራዬን ዐይቶ፣ ልፋቴን ትመልክቶ ትናንት ሌሊት ገሠጸህ።” 43 ላባም ለያዕቆብ እንዲህ ሲል መለሰ፤ “እነዚህ ሴቶች የእኔው ልጆች ናቸው፤ ልጆቻቸውም የእኔ ናቸው፤ እነዚህም መንጋዎች የእኔ ናቸው፤ ይህ የምታየው ሁሉ የራሴ ነው፤ ታዲያ በእነዚህ ሴቶች ልጆቼና በወለዷቸው ልጆቻቸው ላይ ዛሬ ምን ማድረግ እችላለሁ? 44 በል አሁን ቃል ኪዳን እንጋባ፤ ኪዳኑም በአንተና በእኔ መካከል ምስክር ይሁን።” 45 ያዕቆብም ድንጋይ ውስዶ ሐውልት አድርጎ አቆመው፤ 46 ከዚያም ዘመዶቹን “ድንጋይ ሰብስቡ” አላቸው። እነርሱም ድንጋይ እያመጡ ከመሩ፤ በክምሩም አጠገብ ምግብ በሉ። 47 ላባም ክምር ድንጋዩን ይጋርሠሀዱታ ብሎ ጠራው፤ ያዕቆብ ደግሞ ገለዓድ አለው። 48 ላባም “ይህ ክምር ድንጋይ በእኔና በአንተ መካከል ዛሬ ምስክር ነው” አለው። ገለዓድ ተብሎ የተጠራውም በዚሁ ምክንያት ነው፤ 49 ደግሞም ምጽጳ ተባለ ምክንያቱም ላባ እንዲህ ብሎአልና፤ “እንግዲህ ከዚህ በምንለያይበት ጊዜ እግዚአብሔር እኔንና አንተን ይጠብቀን፤ 50 ልጆቼን ብትበድላቸው ወይም ሌሎችን በላያቸው ብታገባ፣ ማንም ከእኛ ጋር ባይኖርም እንኳ እግዚአብሔር በአንተና በእኔ መካከል ምስክር መሆኑን አትርሳ።” 51 ላባም ያዕቆብን እንዲህ አለው፦ “ክምር ድንጋዩ እነሆ፤ በአንተና በእኔ መካካል ያቆምሁትም ሐውልት እነሆ፤ 52 ይህን ክምር ድንጋይ አልፌ አንተን ለማጥቃት ላልመጣ፣ አንተም ይህን ክምር ድንጋይና ይህን ሐውልት አልፈህ እኔን ለማጥቃት ላትመጣ፤ ይህ ክምር ድንጋይ ምስክር ነው፤ ይህም ሐውልት ምስክር ነው። 53 የአብርሃም አምላክ፣ የናኮር አምላክ፣ የአባታቸውም አምላክ በመካከላችን ይፍረድ።” ስለዚህ ያዕቆብ አባቱ ይስሐቅ በሚፈራው በእግዚአብሔር ማለ። 54 ያዕቆብ በኮረብታማው አገር ላይ መሥዋዕት አቀረበ፤ ዘመዶቹንም ምግብ እንዲበሉ ጋበዛቸው፤ እነርሱም ከበሉ በኋላ እዚያው አደሩ። 55 በማግስቱም ማለዳ ላባ የልጅ ልጆቹን እንዲሁም ሴቶች ልጆችን ስሞ መረቃቸው፤ ከዚያም ወደ አገሩ ተመለሰ።