30

1 ራሔል ለያዕቆብ አንድም ልጅ እንዳልወለደችለት ባየች ጊዜ በእኅቷ ቀናች። ያዕቆብንም፣ “ልጅ ስጠኝ አለበለዚያ እሞታለሁ” አለችው። 2 ያዕቆብም ራሔልን ተቆጥቶ፤ “እኔ የሆድሽን ፍሬ በነሳሽ በእግዚአብሔር ቦታ ነኝን?” አላት። 3 እርሷም፣ “እነሆ፣ አገልጋዬ ባላ አለችልህ፣ ልጆች እንድትወልድልኝና እኔም ደግሞ በእርሷ አማካይነት ልጆች እንዳገኝ ከእርሷ ጋር ተኛ” አለችው። 4 ስለዚህ ባላን እንደሚስት አድርጋ ሰጠችው፤ ያዕቆብም ከእርሷ ጋር የግብረ-ሥጋ ግንኙነት አደረገ። 5 ባላም አረገዘችና ወንድ ልጅ ወለደችለት። 6 ራሔልም፦ “እግዚአብሔር ፈረደልኝ፣ ልመናዬንም ሰምቶ ወንድ ልጅ ሰጥቶኛል” አለች። ስለዚህ ስሙን ዳን ብላ ጠራችው። 7 የራሔል አገልጋይ ባላ ዳግመኛ አረገዘችና ለያዕቆብ ሁለተኛ ወንድ ልጅ ወለደች። 8 ከእኅቴ ጋር ብርቱ ትግል ታግዬ አሸነፍኋት” አለች። ስለዚህ ስሙን ንፍታሌም ብላ ጠራችው። 9 ልያም ልጅ መውለድ ማቆሟን እንደተረዳች፣ አገልጋይዋን ዘለፋን ሚስት እንድትሆነው ለያዕቆብ ሰጠችው። 10 የልያ አገልጋይ ዘለፋም ለያዕቆብ ወንድ ልጅ ወለደችለት፣ 11 ልያም፣ “እንዴት የታደልሁ ነኝ!” ስትል ስሙን ጋድ ብላ ጠራችው። 12 የልያም አገልጋይ ዘለፋ ለያዕቆብ ሁለተኛ ልጅ ወለደችለት፤ 13 ልያም፣ “እጅግ ደስ ብሎኛል፣ ከእንግዲህ ወዲያ ሴቶች ‘ደስተኛዋ’ ይሉኛል አለች፤ ስሙንም ‘አሴር’ ብላ ጠራችው። 14 በስንዴ መከር ወራት ሮቤል ወደ ዱር ሄዶ እንኮይ አገኘ፤ ለእናቱ ለልያም አመጣላት፤ ራሔልም ልያን፣ “እባክሽን ልጅሽ ካመጣልሽ እንኮይ ስጪኝ” አለቻት። 15 ልያም፦ “ባሌን የቀማሽኝ አነሰና የልጄን እንኮይ ደግሞ ልትወስጂ አማረሽ?” አለቻት። ራሔልም፣ “ስለልጅሽ እንኮይ ዛሬ ያዕቆብ ከአንቺ ጋር ይደር” አለቻት። 16 በዚያ ምሽት ያዕቆብ ከእርሻ ሲመለስ፣ ልያ ወጥታ ተቀበለችውና፣ “በልጄ እንኮይ ስለተከራየሁህ የዛሬው አዳርህ ከእኔ ጋር ነው” አለችው። ያዕቆብም በዚያች ሌሊት ከእርሷ ጋር አደረ። 17 እግዚአብሔር የልያን ጸሎት ሰማ፣ ስለዚህ አረገዘችና ለያዕቆብ አምስተኛውን ወንድ ልጅ ወለደችለት። 18 ልያም፦ “አገልጋዬን ለባሌ በመስጠቴ እግዚአብሔር ደመወዜን ከፈለኝ” አለች። ስሙንም ይሳኮር አለችው። 19 ልያ አሁንም ደግማ ፀነሰች፤ ለያዕቆብም ስድስተኛውን ወንድ ልጅ ወለደች። 20 እርሷም፣ “እግዚአብሔር በከበረ ስጦታ አድሎኛል፣ ስድስት ወንዶች ልጆች ስለወለድሁለት ከእንግዲህ ባሌ አክብሮ ይይዘኛል” አለች፤ ስሙንም ዛብሎን አለችው። 21 ከዚያም በኋላ ሴት ልጅ ወለደች ስምዋንም ዲና አለቻት። 22 እግዚአብሔርም ራሔልን አሰበ፤ ጸሎትዋንም ሰምቶ ልጅ እንድትወልድ አደረጋት፤ 23 አርግዛም ወንድ ልጅ ወለደችና፣ “እግዚአብሔር ዕፍረቴን አስወገደልኝ” አለች፤ 24 ደግሞም ሌላ ወንድ ልጅ ይጨምርልኝ ስትል ስሙን ዮሴፍ ብላ ጠራችው። 25 ራሔል ዮሴፍን ከወለደች በኋላ ያዕቆብ ላባን እንዲህ አለው፦ “ወደ ተወለድሁበት አገር እንድመለስ አሰናብተኝ፤ 26 አንተን በማገልገል ያገኘኋቸውን ሚስቶቼንና ልጆቼን ስጠኝና ልሂድ፤ ምን ያህል አገልግሎት እንዳበረከትኩልህ ታውቃለህ።” 27 ላባም፣ “በአንተ ምክንያት እግዚአብሔር እንደባረከኝ በንግርት መረዳቴን ልነግርህ እወዳለሁ፤ 28 የምትፈልገውን ደመወዝ ንገረኝና እከፍልሃለሁ” አለው። 29 ያዕቆብም እንዲህ አለው፦ “እንዴት እንዳገለገልሁህና የከብትህም መንጋ በእኔ ጠባቂነት እንዴት እንደረባልህ አንተ ታውቃለህ፤ 30 እኔ ከመምጣቴ በፊት ጥቂት የነበሩት መንጋዎችህ አሁን እጅግ በዝተዋል፤ በተሰማራሁበት ሁሉ እግዚአብሔር በረከቱን አብዝቶልሃል። ታዲያ፣ ለራሴ ቤት የሚያስፈልገኝን የማቀርበው መቼ ነው?” 31 ላባም፣ “ታዲያ ምን ያህል ልክፈልህ?” ብሎ ጠየቀው። ያዕቆብም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “እኔ የምልህን አንድ ነገር ብቻ ብታደርግልኝ መንጋህን ማሰማራቴንና መጠበቄን እቀጥላልሁ፤ 32 ዛሬ በመንጋዎችህ መካከል ልለፍና ዝንጉርጉርና ነቁጣ ጥቁርም የሆኑትን በጎች ሁሉ ልለይ፤ እንዲሁም ነቁጣና ዝንጉርጉር የሆኑትን ፍየሎች እመርጣለሁ፤ እነርሱም ደመወዜ ይሆናሉ፤ 33 ወደፊት ደመወዜን ለመቆጣጠር በምትመጣበት ጊዜ ታማኝነቴ ይታወቃል፤ ደመወዜን ለመቆጣጠር ስትመጣ ዝንጉርጉር ያልሆነ ወይም ነቁጣ የሌለበት ፍየል ብታገኝ፣ እንዲሁም ጥቁር ያልሆነ በግ ብታገኝ የተሰረቀ መሆኑን መረዳት ትችላልህ” አለው። 34 ላባም፣ “እሺ አንተ ባልከው እስማማለሁ” አለ። 35 ነገር ግን በዚያኑ ዕለት ከተባት ፍየሎች ሽመልመሌ የሆኑትን ወይም ነቁጣ ያለባቸውን ሁሉ እንዲሁም ከእንስት ፍየሎች ነቁጣ ያለባቸውን ዝንጉርጉር የሆኑትን ሁሉ መረጠ፤ ደግሞም ጥቋቁር የሆኑትንም በጎች ሁሉ ለየና ወንዶች ልጆቹን አስጠበቃቸው። 36 ከዚህ በኋላ ላባ መንጋውን ነድቶ የሦስት ቀን መንገድ ያህል ከያዕቆብ ርቆ ሄደ፤ ያዕቆብም የቀሩትን የላባን መንጋዎች መጠበቁን ቀጠለ። 37 ያዕቆብም ልብን፣ ለውዝና ኤርሞን ከሚባሉ ዛፎች እርጥብ በትሮችን ወሰደ፤ በበትሮቹ ያለው ነጭ እንዲታይ ሽመልመሌ አድርጎ ላጣቸው፤ 38 መንጋዎቹ ውሃ ለመጠጣት ሲመጡ ከፊት ለፊት እንዲያዩአቸው የተላጡትን በትሮች በውሃ ማጠጫዎቹ ውስጥ አደረጋቸው። መንጎቹም ስሜታቸው ሲነሣሣና ውሃ ለመጠጣት ሲመጡ፣ 39 በትሮቹን ፊት ለፊት እያዩ ይሳረሩ ነበር፤ ሽመልመሌ፣ ዝንጉርጉርና ነቁጣ የጣለባቸውንም ግልገሎች ወለዱ። 40 ያዕቆብ እነዚህን ግልገሎች ለብቻ ለየ፤ የቀሩትን ግን ዝንጉርጉርና ጥቁር በሆኑት በላባ መጋዎች ፊት ለፊት አቆማቸው፤ በዚህ ዓይነት የራሱን መንጋ ከላባ መንጋ ጋር ሳይቀላቅል ለብቻ አቆማቸው። 41 ያዕቆብም ብርቱ እንስቶች አውራ ፈልገው በሚቅበጠበጡበት ጊዜ በትሮቹ አቅራቢያ እንዲጠቁ በትሮቹን በውሃ ገንዳዎች ውስጥ ፊት ለፊታቸው ያስቀምጥ ነበር፤ 42 ደካማ በሆኑት እንስቶች ፊት ግን በትሮቹን አያስቀምጥም ነበር፤ ስለዚህ ደካሞቹ ለላባ ሲሆኑ፣ ብርቱዎቹ ለያዕቆብ ሆኑ። 43 በዚህም ሁኔታ ያዕቆብ እጅግ ባለጸጋ ሆነ፤ ብዙ መንጋዎች፤ ሴቶችና ወንዶች አገልጋዮች፣ ብዙ ግመሎችና አህዮችም ነበሩት።