ምዕራፍ 3

1 እናንተ ማስተዋል የጎደላችሁ የገላቲያ ሰዎች ማነው በክፉ ዓይኑ ያያችሁ፥ ክርስቶስ እንደተሰቀል ሆኖ በፊታችሁ ተስሎ አልነበረምን? 2 ይህን ብቻ ከእናንተ ማወቅ እፈልጋለሁ። መንፈስ ቅዱስን የተቀበላችሁት በህግ ሥራ ነው ወይስ የሰማችሁትን በማመናችሁ? 3 ይህን ያህል ሞኞች ናችሁ እንዴ፥ በመንፈስ ጀምራችሁ በሥጋ ትጨርሳላችሁ? 4 በእርግጥ ይህ ከንቱ ከተባለ ያን ሁሉ መከራ የተቀብላችሁት በከንቱ ነውን? 5 መንፈስ ቅዱስን የሰጣችሁና በመካከላችሁ ኃይለኛ ነገርን ያደረገው እርሱ ይህን ያደረገው በህግ ሥራ ነው ወይስ ከእምነት በሆነ እምነታችሁ ነው? 6 ልክ አብርሀም «እንዳመነና እምነቱ እንደ ፅድቅ እንደተቆጠረለት» 7 የሚያምኑ ሁሉ የአብርሀም ልጆች እንደሆኑ አስተውሉ። 8 ቅዱሳት መፅሀፍት እግዚአብሔር አህዛብን እንደሚያፀድቅ አስቀድመው አመልክተዋል። ወንጌል « አህዛብ ሁሉ በአንተ ይባረካሉ» ተብሎ በመጀመሪያ ለአብርሀም ተሰብኳል። 9 ስለዚህም የሚያምኑ እምነት ከነበረው ከአብርሀም ጋር የተባረኩ ናቸው። 10 «ህግን ሁሉ ይፈፅም ዘንድ ለህግ የማይታዘዝ ሁሉ የተረገመ ነው» ተብሎ ተፅፎአልና በህግ ስራ የሚታመን ሁሉ በእርግማን ስር ነው። 11 «ጻድቅ በእምነት ይኖራልና» እግዚአብሔር ማንንም በህግ እንደማያጸድቅ ግልጽ ነው። 12 ህግ ከእምነት የመነጨ አይደለም፥ ይልቁኑም «በህግ ውስጥ ያሉትን እነዚያን ነገሮች የሚያደርግ በህግ ይኖራል» 13 «በእንጨት ላይ የሚሰቀል የተረገመ ነው» ተብሎ በተጻፈው መሰረት እርሱ ስለኛ እርግማን በመሆን ከህግ እርግማን ዋጀን። 14 የዚህ ተግባር ዓላማ የመንፈስ ቅዱስን ተስፋ በእምነት እንቀበል ዘንድ በአብርሀም ላይ የነበረው በረከት በክርስቶስ ኢየሱስ በኩል በአህዛብም ላይ እንዲሆን ነው። 15 የምናገረው በሰው ቋንቋ ነው። ልክ በሰዎች መካከል እንደተደረገ ውል ማንም ከዚህ ሊቀንስ ወይም ሊጨምር አይችልም። 16 እንግዲህ ተስፋዎቹ የተነገሩት ለአብርሀምና ለዘሩ ነው። ብዙ ሰዎችን እንደሚያመለክት «ለዘሮቹ» አላለም። ነገር ግን አንድ መሆኑን በሚገልጽ መልኩ«ለዘሩ» ብሎ ይናገራል። ያም ለዘሩ የተባለለት ክርስቶስ ነው። 17 እንግዲህ እንዲህ ልበል። አስቀድሞ በእግዚአብሔር የተረጋገጠው ቃል ኪዳን ተስፋ ከ430 ዓመት በኋላ በተሰጠ ህግ አልተሻረም። 18 ምክንያቱም ውርሱ በህግ የመጣ ቢሆን ኖሮ በተስፋ በኩል ባልመጣ ነበር፥ ነገር ግን እግዚአብሔር ለአብርሃም በተስፋ አማካኝነት ርስትን እንዲያው ሰጠው። 19 ታዲያ ህግ ለምን አስፈለገ? የአብርሃም ዘር ተስፋ ወደተሰጣቸው እስኪመጣ ድረስ በመተላለፍ ምክንያት ህግ ተሰጠ፤ ህጉ በመካከለኛ አማካኝነት በመላዕክት አማካኝነት ተግባራዊ ሆኗል። 20 መካከለኛ ሲል ከአንድ ሰው በላይ እንደሆነ ያመለክታል፥ እግዚአብሔር ግን አንድ ነው። 21 ታዲያ ህግ የእግዚአብሔርን ተስፋ ይቃረናል ማለት ነው? በፍጹም አይደለም። ህይወትን ሊሰጥ የሚችል ህግ ተሰጥቶ ቢሆን ኖሮ በእርግጠኝነት ጽድቅ በህግ በኩል ይመጣ ነበር። 22 ነገር ግን ይልቁኑ መጽሀፍ ሁሉን ነገር ከኃጢአት በታች እስርኛ አድርጓል። ስለዚህም እኛን በክርስቶስ ኢየሱስ ለማዳን እግዚአብሔር የሰጠው ተስፋ ለሚያምኑ ተሰጠ። 23 ነገር ግን በክርስቶስ ማመን ከመምጣቱ በፊት እምነት እስከተገለጠበት ጊዜ ድረስ በህግ ታስረንና ታግደን ነበር። 24 ስለዚህ በእምነት እንድንጸድቅ ህግ ወደ ክርስቶስ ዘመን የሚያደርሰን ሞግዚት ሆነ። 25 አሁን እምነት ስለመጣ ከዚህ በኋላ በሞግዚት ሥር አይደለንም። 26 ምክንያቱም ሁላችሁም በክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁ። 27 በክርስቶስ ስም የተጠምቃችሁ ሁላችሁ ክርስቶስን ለብሳችሁታል። 28 ሁላችሁ በክርስቶስ አንድ ስለሆናችሁ በዚህ ጉዳይ በአይሁድና በግሪክ ሰዎች፥ በባሪያና ነጻ በሆነ፥በሴትና በወንድ መካከል ልዩነት የለም። 29 እንግዲህ የክርስቶስ ከሆናችሁ የአብርሀም ዘሮች እንደተስፋ ቃሉም ወራሾች ናችሁ።