ምዕራፍ 5

1 ምድራዊው መኖሪያችን ቢፈርስ እንኳ በሰማይ በሰው እጅ ያልተሰራ ዘላለማዊ ቤት በእግዚአብሔር እንደተሰራልን እናውቃለን። 2 ድንኳን ውስጥ ሆነን እንቃትታለን፥ሰማያዊ መኖሪያችንንም ልንለብስ እንናፍቃለን። 3 ምክንያቱም ያን ለብሰን ስንገኝ ራቁታችንን ሆነን አንገኝም ። 4 በርግጥ በዚህ ድንኳን ውስጥ ሆነን ከብዶን እንቃትታለን፤ምክንያቱ ደግሞ ሟች የሆነው ሰውነት በህይወት መዋጥ ስላለበት እኛም ለብሰን እንጂ ራቁታችንን መሆን አንፈልግም። 5 ወደ ፊት ሊመጣ ላለው የመንፈሱን ዋስትና የሰጠን ለዚህም ያዘጋጀን እግዚአብሔር ነው። 6 እንግዲህ በሰውነታችን በዚህ ምድር በምንኖርበት ጊዜ በሰማይ ካለው ጌታ ርቀን እንዳለን ይህን እርግጠኛ ሁኑ 7 ምክንያቱም በእምነት እንጂ በማየት አንመላለስምና። 8 ስለዚህ ይህ ድፍረት አለን፤ከሰውነታችን ተለይተን ከጌታ ጋር በሰማይ ቤት መሆንን እንመርጣለን። 9 ስለሆነም በምድርም ብንሆን ወይም ከምድር ብንለይ ግባችን እርሱን ማስደሰት ነው። 10 እያንዳንዳችን በሰውነታችን በዚህ ምድር ላይ የሰራነውን መልካምም ሆነ ክፉ እንቀበል ዘንድ ሁላችን በክርስቶስ የፍርድ ወንበር ፊት መቅረባችን ግድ ነው። 11 እንግዲህ ጌታን መፍራት ምን ማለት እንደሆን ስለምናውቅ ሰዎችን ግድ እንላለን። ማንነታችን በእግዚአብሔር ፊት የተገለጠ ስለሆነ ለናንተም ህሊና ግልፅ እንደሚሆን ተስፋ አለኝ። 12 ራሳችንን ደግመን እንድታወድሱን አናቀርብላችሁም፥ ሆኖም በልብ ሳይሆን በውጫዊው መልክ ለሚመኩ መልስ መስጠት እንዲቻላችሁ እኛን ምክንያት አድርጋችሁ እንድትመኩ እናስታውቃችኋለን። 13 እንደ እብድ ቢያረገን፥ ለእግዚአብሔር ነው፤እንደ ባለአዕምሮ ብንሆን ደግሞ ለእናንተ ስንል ነው። 14 የክርስቶስ ፍቅር ግድ ይለናል፥ በዚህ ነገር እርግጠኞች ነን፡አንዱ ሰው ስለሁሉ ሞተ፥ ስለሆነም ሁሉም ሞቱ ማለት ነው። 15 በህይወት ያሉትም ስለእነርሱ ለሞተውና ለተነሳው እንጂ ለራሳቸው እንዳይኖሩ ክርስቶስ ስለሁሉ ሞተ። 16 ስለዚህም ምክንያት ክርስቶስን ከዚህ ቀደም በሰዋዊ መንገድ አይተነው ቢሆን፥ካሁን ጀምሮ ማንንም በሰዋዊ መስፈርት አንፈርድም። በማንም ላይ ከዚህ በኋል በዚህ መንገድ አንፈርድም። 17 ስለሆነም ማንም በክርስቶስ ውስጥ ቢሆን እርሱ አዲስ ፍጥረት ነው። አሮጌ ነገሮች አልፈዋል። ተመልከቱ፥ ሁሉ አዲስ ሆኗል። 18 እነዚህ ነገሮች ሁሉ የሆኑት እኛን በክርስቶስ ከራሱ ጋር ባስታረቀንና የዕርቅ አገልግሎት በሰጠን በእግዚአብሔር ነው። 19 እግዚአብሔርም በደላቸውን ሳይቆጥርባቸው ዓለሙን በክርስቶስ ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበር። እኛንም ለዚህ የዕርቅ መልዕክት ታማኝ አድርጎ ሾመን። 20 ስለዚህም እግዚአብሔር በእኛ ሆኖ ልመናውን እንደሚያቀርብ፥ የክርስቶስ ተወካዮች ሆነን ተሹመናል። ከእናንተም ጋር በመሆን ስለ ክርስቶስ "ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ!" ብለን ልመና እናቀርባለን። 21 እኛም በእርሱ የእግዚአብሔር ፅድቅ እንድንሆን ሃጢያት ሰርቶ የማያውቀውን ክርስቶስን እግዚአብሔር የሃጢያት መስዋዕት አደረገው።