ምዕራፍ 4

1 እንግዲህ፥ይህ አገልግሎት ስላለን እንዲሁም ምህረት እንደተቀበልን መጠን፥ ተስፋ አንቆርጥም። 2 በዚያ ፈንታ ግን አሳፋሪ እና ድብቅ የሆኑ መንገዶችን ክደናል። የተንኮል ህይወት አንኖርም፥የእግዚአብሔርንም ቃል ያለ አግባብ አንጠቀምበትም። እውነትንም እየተናገርን ራሳችንን ለሰው ሁሉ ህሊና በእግዚአብሔር ፊት እናቀርባለን። 3 ሆኖም ግን ወንጌላችን የተሸፈነ ቢሆን፥የተሸፈነው ለሚጠፉት ሰዎች ብቻ ነው። 4 በእነርሱ ሁኔታ ታዲያ የዚህ ዓለም አምላክ የማያምን አዕምሮዋቸውን አሳውሮታል። በዚህም የእግዚአብሔር መልክ የሆነውን የክርስቶስን የክብር ወንጌል ብርሃን እንዳያዩ አደረጋቸው። 5 ክርስቶስ ኢየሱስ ጌታ እንደሆነ እንጂ ራሳችንን አንሰብክም፥እንዲሁም ስለ ኢየሱስ ስንል የእናንተ አገልጋዮች ነን። 6 ውስጥ ብርሃን ይብራ" ያለው ራሱ እግዚአብሔር ነው፤እናም በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት የእግዚአብሔር ክብር የእውቀት ብርሃን እንዲሰጠን በልባችን ውስጥ አበራልን። 7 ነገር ግን እጅግ ታላቅ የሆነው ሃይሉ ከእግዚአብሔር እንጂ ከእኛ እንዳልሆነ ለማሳየት ይህ ሃብት በሸክላ ዕቃ ውስጥ አለን። 8 በሁሉ መንገድ መከራን እንቀበላለን፥ሆኖም በዚያ አንዋጥም። እናመነታለን ነገር ግን ተስፋ በማጣት አንረበሽም። 9 ቢሆንም ግን ተረስተን አንቀርም። 10 የኢየሱስ ህይወት በሰውነታችን እንዲገለጥ የእርሱን ሞት ሁልጊዜ በሰውነታችን እንሸከማለን። 11 ይህም የኢየሱስ ህይወት በሰብዓዊ ሰውነቶቻችን እንዲገለጥ እኛ ህያዋን የሆንን በየዕለቱ ስለ ኢየሱስ ምክንያት ለሞት ታልፈን እንሰጣለን። 12 በዚህም ምክንያት ሞቱ በእኛ፥ ህይወቱም በእናንተ ይሰራል። 13 ነገር ግን "አመንሁ ስለዚህም ተናገርሁ"ተብሎ እንደተፃፈ፡ ሁላችንም አንድ አይነት የእምነት መንፈስ አለን። ስለምናምንም እንናገራለን። 14 ጌታ ኢየሱስን ከሞት ያስነሳው እኛንም ከእርሱ ጋር ያስነሳናል። ከእናንተም ጋር ወደ ፊቱ እንዲያመጣን እናውቃለን። 15 የሚሆነው ለእናንተ ጥቅም ሲሆን ፀጋ ለብዙዎች ሲበዛ ለእግዚአብሔር ክብር የሚሆን ምስጋናም ይጨምራል። 16 ስለዚህም ተስፋ አንቆርጥም። ምንም እንኳ ውጫዊው ማንነታችን እየደከም ቢመጣም ውስጣዊው ማንነታችን ዕለት በየዕለት ይታደሳል። 17 ይህ ጊዜያዊ፣ ቀላል መከራችን መለኪያ ለሌለው፥ ለላቀው ዘላለማዊ ክብር የሚያዘጋጀን ነው። 18 የሚታዩትን ነገሮች ሳይሆን የማይታዩትን ነገሮች እንመለከታለን። የምናያቸው ነገሮች ጊዜያዊ ሲሆኑ የማይታዩት ነገሮች ግን ዘላለማዊ ናቸው።