ምዕራፍ 3

1 ራሳችንን እንደገና ልናወድስ እንጀምራለንን? አንዳንድ ሰዎች እንደሚያደርጉት ለናንተም ሆነ ከእናንተ የድጋፍ ደብዳቤ ያስፈልገን ይሆን? አያስፈልገንም። 2 እናንተ ራሳችሁ በልባችን ላይ የተፃፋችሁ፥በሁሉም ሰዎች የምትታውቁ እና የምትነበቡ የድጋፍ ደብዳቤያችን ናችሁ። 3 በእኛ የቀረባችሁ የክርስቶስ መልዕክት ከመሆናችሁም በላይ በህያው የእግዚአብሔር መንፈስ እንጂ በቀለም ያልተፃፋችሁ፤በሰዎች የልብ ፅላት ላይ እንጂ በድንጋይ ፅላት ላይ ያልተቀረፃችሁ ናችሁ። 4 እንግዲህ በክርስቶስ በኩል በእግዚአብሔር ላይ ይህ መታመን አለን። 5 ከእኛ የሆነ ብለን ልናስበው የምንችል አንዳች ችሎታ የለንም፤ነገር ግን ብቃታችን ከእግዚአብሔር ነው። 6 እርሱም የአዲስ ኪዳን አገልጋዮች አደረገን። ይህ ኪዳን የፊደል ሳይሆን የመንፈስ ነው። ምክንያቱም ፊደል ይገድላል፣ መንፈስ ግን ህይወትን ይሰጣል። 7 የእስራኤል ህዝብ ከፊቱ ክብር የተነሳ እያደር የሚደበዝዘውን የሙሴን ፊት መመልከት እስኪያቅታቸው ድረስ በፊደላት በድንጋይ ላይ የተቀረፀው የሞት አገልግሎት በክብር ከሆነ፤ 8 የመንፈስ አገልግሎት እጅግ በክብር አይልቅምን? 9 የኩነኔ አገልግሎት ክብር ከነበረው፥የፅድቅ አገልግሎት እንደምን በክብር ይብዛ! 10 በርግጥም ቀድሞ በክብር የነበረው ከሱ በሚበልጥ ክብር ተሽሯል። 11 አላፊው በክብር ከሆነ ፀንቶ የሚኖረው በክብር እንዴት ይበልጥ! 12 እንግዲያውስ እንዲህ ያለ ትምክህት ስላለን እጅግ በድፍረት እንናገራለን። 13 እኛ የእስራኤል ህዝቦች የሚያልፈውን ክብር ትኩር ብለው መመልከት እንዳልቻሉት፤ ፊቱን በመሸፈኛ እንደ ከለለው እንደ ሙሴ አይደለንም። 14 ሆኖም ግን አእምሮዋቸው ተሸፈነባቸው። እስከዛሬም አሮጌው ኪዳን ሲነበብ ያው መሸፈኛ ይኖራል፤ሊገለጥም አይችልም፤ ምክንያቱም ሊወገድ የሚችለው በክርስቶስ ነው። 15 ሆኖም ግን እስከዛሬ ድረስ የሙሴ ህግ ሲነበብ በልባቸው ላይ መሸፈኛው ይኖራል። 16 ሰው ግን ወደ ጌታ መለስ ሲል ፥መሸፈኛው ይነሳል። 17 ጌታም መንፈስ ነው፤የጌታም መንፈስ ባለበት ነፃነት አለ። 18 እኛም ሁላችን ባልተሸፈነ ፊት የጌታን ክብር እያየን እርሱን ወደሚመስል ከአንድ ክብር ደረጃ ወደ ሌላ ክብር ደረጃ እንለወጣለን፤ይህም የሚሆነው መንፈስ ከሆነው ጌታ ነው።