ምዕራፍ 2

1 ስለዚህም በበኩሌ እንደገና ላስከፋችሁ ተመልሼ መምጣት አልፈለግሁም። 2 ባስከፋችሁ እንኳ ሊያስደስተኝ የሚችለው ያው ያስከፋሁት ሰው አይደለምን? 3 እንደፃፍኩላችሁ ወደ እናንተ በመጣሁ ጊዜ ደስ ሊያሰኙኝ የሚገባችው ሰዎች እንዳያሳዝኑኝ ነው። ስለሁላችሁም እርግጠኛ የምሆንበት በእኔ ያለ ደስታ በተመሳሳይ መልኩ በእናንተም ዘንድ ያለ መሆኑ ነው። 4 የፃፍኩላችሁም በታላቅ ጭንቀት፥ በልብ መናወጥ እንዲሁም በብዙ እንባ ነበር፥ ምክንያቱ ደግሞ ለናንተ ያለኝን ጥልቅ ፍቅር እንድታውቁ እንጂ እንዳላሳዝናችሁ ነው። 5 ማንም ያሳዘነ ሰው ቢኖር እኔን ብቻ ያሳዘነ ሳይሆን በተወሰነ መልኩ ሁላችሁንም ነው። 6 ለዚያም ሰው በብዙዎች የደረሰበት ቅጣት ይበቃዋል። 7 ግን ይህን ሰው በብዙ ሐዘን እንዳይዋጥ ከመቅጣት ይልቅ ይቅር ልትሉትና ልታፅናኑት ይገባል። 8 ስለዚህም ለዚህ ሰው ፍቅራችሁን በይፋ እንድታረጋግጡለት አደፋፍራችኋለሁ። 9 የፃፍኩላችሁ በሁሉ ነገር ታዛዦች መሆናችሁን እንድፈትንና እንዳውቅ ነው። 10 አንድን ሰው ይቅር ብትሉት፣ እኔም ያንን ሰው ይቅር እለዋለሁ። እኔ ይቅር የምለው አንዳች ነገር ቢኖር ይቅርታ የማደርግለት በክርስቶስ ፊት ስለ እናንተ ስል ነው። 11 ይህን የማደርገውም ሰይጣን እንዳያታልለን ነው። ምክንያቱም የርሱን እቅድ አንስተውምና። 12 ምንም እንኳ ወደ ጥሮአዳ ስመጣ የክርስቶስን ወንጌል ለመስበክ በጌታ በር ተከፍቶልኝ ነበር። ሆኖም ወንድሜን ቲቶን በዚያ ስላላገኘሁት በአዕምሮዬ አላረፍኩም ነበር። 13 ስለሆነም እነርሱን ትቼ ወደ መቄዶንያ ተመለስኩ። 14 ነገር ግን ሁልጊዜ በክርስቶስ በድል ለሚመራን፥ ጣፋጭ የእውቀት ሽታ በየስፍራውም ለሚናኘው ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። 15 ምክንያቱም በሚድኑትና በሚጠፉት መካከል ለእግዚአብሔር የክርስቶስ ጣፋጭ ሽታ ነን። 16 ለሚጠፉት ሰዎች፥ለሞት የሚሆን የሞት ሽታ ስንሆን ለሚድኑት ደግሞ ለህይወት የሚሆን የህይወት ሽታ ነን። ለነዚህ ነገሮች የበቃ ማነው? 17 የእግዚአብሔርን ቃል ለትርፋቸው እንድሚነግዱበት እንደ ብዙዎች አይደለንም። በዚያ ፈንታ በክርስቶስ ሆነን በእግዚአብሔር ፊት፥ ከእግዚአብሔር እንደተላክን በቅን ልቦና እንናገራለን።