9

1 ከዚያ በኋላ እግዚአብሔር ኖኅንና ልጆቹን እንዲህ ሲል ባረካቸው፦ “ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሏት፤ 2 አስፈሪነታችሁና አስደንጋጭነታችሁ በእንስሳት፣ በሰማይ ወፎች፣ በደረት በሚሳቡ ተንቀሳቃሽ ፍጡሮችና በባሕር ዓሦች፣ በምድር ላይ በሚገኙ ሕያዋን ፍጡራን ሁሉ ላይ ይሁን። ሁሉም በሥልጣናችሁ ሥር ይሁኑ። 3 ሕያውና ተንቀሳቃሽ ፍጡር ሁሉ ምግብ ይሁናችሁ፣ ለምለሙን ዕፅዋት እንደሰጠኋችሁ፣ አሁን ደግሞ ሁሉን ሰጠኋችሁ። 4 ነገር ግን ሕይወቱ ማለት ደሙ ገና በውስጡ ያለበትን ሥጋ አትብሉ። 5 ሰውን የገደለ ሁሉ ስለሟቹ ደም ተጠያቂ ነው፤ የሟቹን ሰው ደም ከገዳዩ ከእንስሳም ይሁን ከሰው እሻለሁ። 6 የሰውን ደም የሚያፈስ ሁሉ ደሙ በሰው እጅ ይፈሳል፤ በእግዚአብሔር አምሳል እግዚአብሔር ሰውን ሠርቶታልና። 7 እናንተ ግን ብዙ ተባዙ፣ ዘራችሁ በምድር ላይ ይብዛ ይንሠራፋም።” 8 ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ለኖኅና ለልጆቹ እንዲህ አላቸው፦ 9 “እነሆ ከእናንተና ከእናንተ በኋላ ከሚመጣው ዘራችሁ ጋር ኪዳኔን እመሠርታለሁ፤ 10 እንዲሁም ከእናንተ ጋር ከነበሩት ሕያዋን ፍጡራን ሁሉ ከወፎች፣ ከእንስሳት ከእናንተ ጋር ከመርከቧ ከወጡት በምድር ላይ ካሉት ሕያዋን ፍጡራን ሁሉ ጋር ኪዳን እገባለሁ። 11 ከእንግዲህ ሕይወት ያለው ፍጡር ሁሉ በጥፋት ውሃ እንደማይጠፋ፣ ዳግመኛም ምድርን የሚያጠፋ ውሃ ከቶ እንደማይመጣ ከእናንተ ጋር ኪዳን እገባለሁ።” 12 እግዚአብሔርም እንዲህ አለ፦ “በእኔና በእናንተ መካከል ከእናንተም ጋር ካሉ ሕያዋን ፍጡራን ሁሉ፣ ከሚመጣው ትውልድ ሁሉ ጋር፣ የማደርገው የኪዳኑ ምልክት ይህ ነው፤ 13 ቀስተ ደመናዬን በደመና ላይ አድርጋለሁ፤ ይህም በእኔና በምድር መካከል ለገባሁት ኪዳን ምልክት ይሆናል። 14 ደመናን በምድር ላይ በጋረድሁና ቀስቴም በደመና ላይ በሚታይበት ጊዜ ሁሉ 15 ከእናንተና ከሕያዋን ፍጡራን ሁሉ ጋር የገባሁትን ኪዳን አስባለሁ፤ ሕይወት ያለውንም ሁሉ ያጠፋ ዘንድ፣ ከእንግዲህ የጥፋት ውሃ ከቶ አይመጣም። 16 ቀስቱ በደመና ላይ ተገልጦ በማይበት ጊዜ ሁሉ በእኔና በምድር ላይ ባሉ ሕያዋን ፍጡራን መካከል ያለውን ዘላለማዊ ኪዳን አስባለሁ።” 17 ከዚያ በኋላም እግዚአብሔር ለኖኅ፦ “ይህ በእኔና በምድር ላይ በሚኖሩ ሕያዋን ሁሉ መካከል የገባሁት ኪዳን ምልክት ነው።” አለው። 18 ከመርከቧ የወጡትም የኖኅ ልጆች ሴም፣ ካምና ያፌት ነበር፤ ካም የከነዓን አባት ነው። 19 እነዚህ ሶስቱ የኖኅ ልጆች ሲሆኑ፣ በምድር ላይ የሚኖሩ ሕዝቦች ሁሉ የተገኙት ከነዚሁ ነው። 20 ኖኅ ገበሬ መሆን ጀመረ፣ ወይንንም ተከለ። 21 ከወይኑም ጠጅ ጠጥቶ ሰከረና በድንኳኑ ውስጥ እርቃኑን ተኛ። 22 የከንዓን አባት ካም የአባቱን ዕርቃነ ሥጋ አየ፤ ወደ ውጭም ወጥቶ ለሁለቱ ወንድሞቹ ነገራቸው። 23 ሴምና ያፌት ግን ልብስ ወስደው በትከሻቸው ላይ አደረጉና የአባታቸውን ዕርቃነ ሥጋ እንዳያዩ ፊታቸውን አዙረው የኋሊት በመሄድ የአባታቸውን ዕርቃነ ሥጋ ሸፈኑ። 24 ኖኅ ከወይን ጠጁ ስካር ሲነቃ ታናሽ ልጁ ያደረገበትን አወቀ። 25 ከዚህም የተነሣ፦ “ከነዓን የተረገመ ይሁን፤ ለወንድሞቹም አገልጋይ ይሁን።” አለ። 26 ደግሞም፦ “የሴም አምላክ የሆነው እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን፣ ከነዓንም የሴም አገልጋይ ይሁን። 27 እግዚአብሔር የያፌትን ግዛት ያስፋ፤ ያፌት በሴም ድንኳኖች ይኑር፤ ከነዓን የያፌት አገልጋይ ይሁን።” አለ። 28 ኖኅ ከጥፋት ውሃ በኋላ 350 ዓመት ኖረ። 29 ኖኅ በአጠቃላይ 950 ዓመት ኖሮ ሞተ።