10

1 የኖኅ ልጆች የሴም፣ የካምና የያፌት ዝርያዎች የሚከተሉት ናቸው። ከጥፋት ውሃም በኋላ ልጆች ተወለዱላቸው። 2 የያፌት ልጆች፦ ጋሜር፣ ማጎግ፣ ማዴ፣ ያዋን፣ ቶቤል፣ ሞሳሕና ቴራስ ነበሩ። 3 የጋሜር ልጆች፦ አስከናዝ፣ ሪፋትና ቴርጋማ ነበሩ። 4 የያዋን ልጆች፦ ኤሊሳ፣ ተርሴስ፣ ኪቲምና ሮዳኢ ነበሩ። 5 ከእነዚህም በየነገዳቸው በየጎሳቸውና በየቋንቋቸው ተከፋፍለው በባሕር ዳርና በደሴቶች በየምድራቸው የሚኖሩ ሕዝቦች ወጡ። 6 የካም ልጆች፦ ኩሽ፣ ምጽራይም፣ ፉጥና ከነዓን ነበሩ። 7 የኩሽ ልጆች፦ ሳባ፣ ኤውላጥ፣ ሰብታ፣ ራዕማና ሰበቀታ ነበሩ። የራዕማ ልጆች፦ ሳባና ድዳን ነበሩ። 8 ኩሽ በምድር ላይ የመጀመሪያው ታላቅ ጦረኛ የነበረው የናምሩድ አባት ነበር። 9 እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ብርቱ አዳኝ ነበር። ስለዚህም፣ “በእግዚአብሔር ፊት እንደ ናምሩድ ብርቱ አዳኝ” ይባል ነበር። 10 የግዛቱም የመጀመሪያ ከተሞች በሰናዖር ምድር የነበሩት፡- ባቢሎን፣ አሬክ፣ አርካድና ካልኔ ነበሩ። 11 ከዚያም ወደ አሦር ምድር ሄደና ነነዌን፣ ርሆቦትን፣ ካላሕን 12 እንዲሁም በነነዌና በካላሕ መካከል የነበረውን ታላቅ ከተማ ሬሴን የተባሉትን ከተሞች መሠረተ። 13 ምጽራይም የሎዳማውያን፣የዐናሚማውያን፣ የላህሚማውያን፣ የነፍታሌማውያን፣ 14 የፈተሩሲማውያንና ፍልስጥኤማውያን የተገኙባቸው የካስሎሂማውያንና የቀፍቶርማውያን አባት ነበር። 15 የከነዓንም የበኩር ልጅ ሲዶን ተከታዩም ሔት ይባሉ ነበር። 16 ሌሎቹም የከነዓን ዝርያዎች ኢያቡሳውያን፣ አሞራውያን፣ ጌርጌሳውያን፣ 17 ኤውያውያንን፣ ዓርቃውያን፣ ሲናውያን፣ 18 ኤርዋዳውያን፣ አርዋዳውያን፣ ደማራውያን፣ ሐማታውያን የሚባሉ ነበሩ። ከጊዜ በኋላ የከነዓን ጎሣዎች በየስፍራው ተሠራጩ። 19 የከነዓን ወሰን ከሲዶና አንሥቶ በጌራራ በኩል ገሞራን አዳማንና ሰቦይን ይዞ እስከ ላሣ ይዘልቃል። 20 እነዚህም በየጎሣቸውና በየቋንቋቸው በየምድራቸውና በየነገዳቸው ይኖሩ የነበሩ የካም ዝርያዎች ነበሩ። 21 ለያፌት ታላቅ ወንድም ለሴም ደግሞ ወንዶች ልጆች ተወለዱለት፤ እርሱም የዔቦር ልጆች ሁሉ ቅድመ አያት ነበር። 22 የሴም ልጆች ኤላም፣ አሦር፣ አርፋክስድ፣ ሉድ፣ አራም ነበሩ። 23 የአራም ልጆች ዑፅ፣ ሁል፣ ጌቴር፣ ሞሶሕ ነበሩ። 24 አርፋክስድ ሳላን ወለደ፤ ሳላም ኤቦርን ወለደ። 25 ዔቦርም ሁለት ወንዶች ልጆችን ወለደ። በዘመኑ ምድር ተከፍላ ስለነበር የአንደኛው ልጅ ስም ፍሌቅ ተባለ፤ ወንድሙም ዮቅጣን ተባለ። 26 ዮቅጣንም የአልሞዳድ፣ የሼሌፍ፥ የሐጸርማዌት፣ የዮራሕ፣ 27 የዐዶራም፣ የኢዛል፣ የዲቅላ፣ 28 የዖባል፣ የአቢማኤል፣ የሳባ፣ 29 የኦፊር፣ የሐዊላና የዮባብ አባት ነበር። እነዚህ ሁሉ የዮቅጣን ዝርያዎች ነበሩ። 30 መኖርያ ስፍራቸውም በስተምሥራቅ ባለው በተራራማው አገር ከሜሻ እስከ ስፋር ይደርስ ነበር። 31 እነዚህም በየጎሣቸውና በየቋንቋቸው በየምድራቸውና በየነገዳቸው ይኖሩ የነበሩ የሴም ዝርያዎች ነበሩ። 32 የኖኅ ወንዶች ልጆች ጎሣዎች እንደ ትውልዳቸው በየነገዳቸው እነዚህ ነበሩ። ከጥፋት ውሃ በኋላ ሕዝቦች በምድር ላይ የተሠራጩት ከእነዚሁ ነበር።