49

1 ያዕቆብ ልጆቹን ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “በአንድነት ተሰብሰቡና ወደፊት የሚገጥማችሁን ነገር ልንገራችሁ፣

2 እናንተ የያዕቆብ ልጆች፣ በአንድነት ተሰብስባችሁ ስሙ፣ አባታችሁ እስራኤል የሚነግራችሁንም አድምጡ።
3 ሮቤል፣ ኃይልና የጎልማሳነት ብርታት በነበረኝ ጊዜ የወለድሁህ የበኩር ልጄ ነህ። ከልጆቼ ሁሉ በክብርና በኃይል የምትበልጥ አንተ ነህ።
4 ይሁን እንጂ እንደ ውሃ የምትዋልል ስለሆንህ የበላይ አለቅነት ለአንተ አይገባም፣ ምክያንቱም የአባትህን መኝታ ደፍረሃል ምንጣፌንም አርክሰሃል።
5 “ስምዖንና ሌዊ ወንድማማቾች ናቸው፣ ዓመፅ ለመፈጸም የጦር መሣሪያዎቻቸውን ያነሳሉ።
6 ወደ ሸንጎአቸው አልግባ፣ ጉባኤያቸው ውስጥ አልገኝ፣ በቁጣ ተነሣስተው ወንዶችን ገድለዋል፣ የበሬዎችንም ቋንጃ እንደፈለጉ ቆራርጠዋል።
7 እጅግ አስፈሪ የሆነ ቁጣቸው፣ ጭከና የተሞላ ንዴታቸው የተረገመ ይሁን፤ በያዕቆብ እበትናቸዋለሁ፣ በመላው እስራኤልም አሠራጫቸዋለሁ።
8 ይሁዳ ወንድሞችህ ያመሰግኑሃል፣ እጅህም የጠላቶችህን አንገት አንቆ ይይዛል፣ የአባትህ ልጆች በፊትህ ተደፍተው ይስግዱልሃል።
9 ይሁዳ እንደ ደቦል አንበሳ ነው፣ ከዐደንህ የምትመለስ ልጄ፣ እንደ አንበሳ ያደፍጣል በምድርም ላይ ይተኛል፤ እንደ እንስት እንበሳም ያደባል፣ ታዲያ ማን ሊቀሰቅሰው ይደፍራል?
10 በትረ መንግስሥት ከይሁዳ እጅ አይወጣም፤ የገዥነት ምርኩዝም ከእግሮቹ መካከል፣ ሕዝቦች ሁሉ የሚታዘዙለት ‘ሴሎ’ እስኪመጣ ድረስ፣ ሕዝቦች ሁሉ ይታዘዙለታል።
11 አህያውን በወይን ግንድ፣ ውርንጫውንም በምርጡ የወይን ሐረግ ቅርንጫፍ ላይ ያስራል፣ ልብሱን በወይን ጠጅ፣ መጎናጸፊያውንም በወይን ጭማቂ ያጥባል።
12 ዓይኖቹ ከወይን ጠጅ የቀሉ፣ ጥርሶቹም ከወተት ይልቅ የነጡ ይሆናሉ።
13 ዛብሎን በባሕር ዳርቻ ይኖራል፣ የመርከቦቹ መጠጊያም ይሆናል፣ ወሰኑም እስከ ሲዶና ይደርሳል።
14 ይሳኮር፣ አጥንተ ብርቱ አህያ በጭነት መካከል የሚተኛ፣ ማረፊያ ቦታው መልካም፣
15 ምድሪቱም አስደሳች መሆኗን ሲያይ፣ ትከሻውን ለሸክም ዝቅ ያደርጋል ከባድ የጉልበት ሥራም ይሠራል።
16 ዳን ከእስራኤል ነገዶች እንደ አንዱ ሆኖ በራሱ ሕዝብ ላይ ይፈርዳል።
17 ዳን የመንገድ ዳር እባብ፣ የመተላለፊያም መንገድ እፉኝት ነው፤ ጋላቢው የኋሊት እንዲወድቅ፣ የፈረሱን ሰኮና ይነክሳል።
18 እግዚአብሔር ሆይ፣ ማዳንህን እጠባበቃለሁ።
19 ጋድን ወራሪዎች አደጋ ይጥሉበታል፣ እርሱ ግን ዱካቸውን ተከታትሎ ብድሩን ይመልሳል።
20 አሴር ማዕደ ሰፊ ይሆናል፤ ለነገሥታትም የሚስማማ ምግብ ያቀርባል።
21 ነጻ እንደተለቀቀች ሚዳቋ ነው፣ የሚያማምሩ ግልገሎች ይኖሩታል።
22 ዮሴፍ፤ ፍሬያማ የወይን ተክል፣ በምንጭ ዳር የተተከለ ወይን ነው። ሐረጎቹ ቅጥርን ያለብሳሉ።
23 ቀስተኞች በብርቱ ያጠቁታል፤ በቀስታቸውም እየነደፉ ያሳድዱታል፤
24 ነገር ግን በያዕቆብ ኃያል አምላክ ክንድ፣ እረኛም በሆነው በእስራኤል አለት ቀስቱ ጸና ጠንካራ ክንዱም ቀልጣፋ ሆነ።
25 አንተን በሚረዳህ በአባትህ አምላክ፣ በሚባርክህ ሁሉን በሚችል አምላክ፣ ከላይ ከሰማይ በሚገኝ ረድኤት፣ ከምድር ጥልቅ በሚገኝ በረከት፣ ከማኅፀንና ከጡት በሚገኝ ምርቃት ይባርክሃል።
26 ከጥንት ተራሮች በረከት፣ ከዘላለም ኮረብቶች ምርቃት ይልቅ፣ የአባትይ በረከት ይበልጣል፤ ይህ ሁሉ በዮሴፍ ራስ ላይ ይውረድ፤ በወንድሞቹ መካከል አለቃ በሆነውም ግንባር ላይ ይረፍ።
27 ብንያም ነጣቂ ተኩላ ነው፤ ያደነውን ማለዳ ይበላል፤ የማረከውን ማታ ያከፋፍላል።

28 እነዚህ ሁሉ ዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች ናቸው። ይህም እያንዳንዳቸውን ተገቢ በሆነው በረከት አባታቸው ሲባርካቸው የተናገረው ቃል ነው። 29 ከዚህ በኋላ ያዕቆብ እንዲህ ሲል አዘዛቸው፤ “እኔ የምሞትበትና ወደ ወገኖቼ የምሰበሰብበት ጊዜ ደርሶአል፤ ስለዚህ በኬጢያዊው በኤፍሮን እርሻ ውስጥ ባለችው ዋሻ ከአባቶቼ ዘንድ ቅበሩኝ፤ 30 ይህንን በከነዓን ምድር በመምሬ አጠገብ በማክፌል እርሻ ውስጥ ያለውን ዋሻ የመቃብር ቦታ እንዲሆን ከኬጢያዊው ኤፍሮን ላይ የገዛው አብርሃም ነው። 31 በዚያ አብርሃምና ሚስቱ ሣራ ተቀብረዋል፤ በዚያ ይስሐቅና ሚስቱ ርብቃ ተቀብረዋል፤ እኔም ልያን የቀበርኋት እዚያው ነው፤ 32 እርሻውና ዋሻው የተገዙት ከኬጢያውያን ላይ ነው።” 33 ያዕቆብ እነዚህን ቃላት ለልጆቹ ተናግሮ እንዳበቃ እግሮቹን በአልጋው ላይ ሰብስቦ የመጨረሻ ትንፋሹን ተንፍሶ ሞተ፣ ወደ ወገኖቹም ተሰበሰበ።