48

1 ከጥቂት ጊዜ በኋላም፣ “አባትህ ታሞአል” ተብሎ ለዮሴፍ ስለተነገረው ሁለቱን ልጆቹን ምናሴንና ኤፍሬምን ይዞ ሄደ። 2 ለያዕቆብ፣ “ልጅህ ዮሴፍ ወደ አንተ መጥቶአል” ተብሎ በተነገረው ጊዜ፣ እስራኤል ተበረታትቶ አልጋው ላይ ተቀመጠ። 3 ያዕቆብም ዮሴፍን እንዲህ አለው፤ “ሁሉን የሚችል አምላክ በከነዓን ምድር ሎዛ በምትባል ቦታ ተገለጠልኝ፤ ባረከኝም፤ 4 እንዲህም አለኝ፤ ‘ፍሬያማ አደርግሃለሁ፣ ዝርያዎችህም ብዙ ሕዝቦች ይሆናሉ፣ ይህችንም ምድር ለዝርያዎችህ ለዘላለም ርስት አድርጌ እሰጣቸዋለሁ’ አለኝ።” 5 ወደዚህ ከመምጣቴ በፊት በግብፅ የወለድሃቸው ሁለቱ ልጆችህ ከእንግዲህ የእኔ ልጆች ሆነው ይቆጠራሉ፤ ሮቤልና ስምዖን ልጆቼ እንደሆኑ ሁሉ፣ ኤፍሬምና ምናሴም ልጆቼ ይሆናሉ። 6 ከእነርሱ በኋላ የሚወለዱልህ ልጆች ግን፣ የአንተ ይሁኑ፤ በርስት ድልድላችው ግን በወንድሞቻቸው ስም ይቆጠራሉ። 7 ከሰሜን ምዕራብ መስጴጦምያ ስመለስ ኤፍራታ ለመድረስ ጥቂት ሲቀረኝ፤ እናትህ ራሔል በከነዓን ምድር ሞታብኝ አዘንሁ። እኔም ወደ ኤፍራታ ማለት ወደ ቤተ ልሔም በሚወስደው መንገድ ዳር ቀበርኋት።”

8 እስራኤልም የዮሴፍን ልጆች ባየ ጊዜ፣ “እነዚህ እነማን ናቸው?” ሲል ጠየቀ፤ 9 ዮሴፍም፣ “እነዚህ እግዚአብሔር የሰጠኝ ልጆች ናቸው” ብሎ መለሰለት፤ እስራኤልም “አቅርባቸውና ልመርቃቸው” አለ። 10 በዚህ ጊዜ እስራኤል ዓይኖቹ በእርጅና ምክንያት በመድከማቸው አጥርቶ ማየት ይሳነው ነበር፤ ስለዚህ ዮሴፍ ልጆቹን አባቱ ዘንድ አቀረባቸው፤ አባቱም ስሞ አቀፋቸው። 11 እስራኤልም ዮሴፍን፣ “ዓይንህን እንደገና ዐያለሁ ብዬ አላሰብኩም ነበር፤ እግዚአብሔር ግን ልጆችህን ጭምር ለማየት አበቃኝ” አለው። 12 ዮሴፍም ልጆቹን ከእስራኤል ጉልበት ፈቀቅ በማድረግ አጎንብሶ በግንባሩ መሬት ላይ ተደፋ። 13 ከዚያም ዮሴፍ ሁለቱን ልጆቹን ይዞ ኤፍሬምን ከራሱ በስተቀኝ ከእስራኤል በስተግራ፣ ምናሴን ደግሞ ከራሱ በስተግራ ከእስራኤል በስተቀኝ በኩል አቀረባቸው። 14 እስራኤል ግን ቀኝ እጁን በታናሹ በኤፍሬም ራስ ላይ አኖረ፣ ግራ እጁንም በቀኝ እጁ ላይ አስተላልፎ በበኩሩ በምናሴ ላይ አኖረ። 15 ከዚህ በኋላ ዮሴፍን ባረከ፤ እንዲህም አለው፤ “አባቶቼ አብርሃምና ይስሐቅ መንገዱን በመከተል ያገለገሉትና ለእኔም እስከ ዛሬ ድረስ በዘመኔ ሁሉ እረኛ የሆነኝ አምላክ፣
16 ከጉዳትም ሁሉ የታደገኝ ምልአክ፣ እርሱ እነዚህን ልጆች ይባርክ፤ እነርሱም በስሜ፣ በአባቶቼ በአብርሃምና በይስሐቅ ስም ይጠሩ፣ በምድር ላይ እጅግ ይብዙ።

17 ዮሴፍ አባቱ ቀኝ እጁን በኤፍሬም ራስ ላይ ማድረጉን ሲያይ ቅር ተሰኘ፤ ከኤፍሬም ራስ ላይ አንስቶ በምናሴ ራስ ላይ ለማኖር የአባቱን እጅ ያዘ፤ 18 ዮሴፍም፣ “አባቴ ሆይ፣ እንዲህ አይደለም በኩሩ ይህኛው ስለሆነ፣ ቀኝ እጅህን እርሱ ራስ ላይ አድርግ” አለው። 19 አባቱ ግን፣ “ዐውቃለሁ፣ ልጄ ዐውቃለሁ፣ እርሱም እኮ ሕዝብ ይሆናል፤ ታላቅም ይሆናል፤ ይሁን እንጂ፣ ታናሽ ወንድሙ ከእርሱ ይበልጣል፤ ዘሮቹም ታላቅ ሕዝቦች ይሆናሉ” ብሎ እምቢ አለው። 20 በዚያን ዕለት ባረካቸው፣ እንዲህም አላቸው፤ “እስራኤላውያን በሚመርቁበት ጊዜ የእናንተን ስም በማስታወስ፤ ‘እግዚአብሔር እንደ ኤፍሬምና እንደ ምናሴ ያድርጋችሁ’ ይላሉ” በዚህ ሁኔታም ኤፍሬምን ከምናሴ አስቀደመው።

21 ከዚህ በኋላ እስራኤል ዮሴፍን እንዲህ አለው፣ እኔ የምሞትበት ጊዜ ተቃርቦአል፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሆናል፤ ወደ አባቶቻችሁም ምድር መልሶ ያገባችኋል። 22 እነሆ በሰይፌና በቀስቴ ከአሞራውያን እጅ የወሰድኋትን ምድር ከወንድሞችህ ድርሻ አብልጬ ለአንተ ሰጥቼሃለሁ።”