37

1 የዕቆብ አባቱ በኖረበት በከነዓን ምድር ተቀመጠ።

2 የያዕቆብ ትውልድ ታሪክ ይህ ነው። ዮሴፍ የዐሥራ ሰባት ዓመት ወጣት በነበረ ጊዜ፣ ከአባቱ ሚስቶች ከባላቅና ከዘለፋ ከተወለዱት ወንድሞቹ ጋር የአባቱን በጎችና ፍየሎች ይጠብቅ ነበር። እርሱም ስለወንድሞቹ ድርጊት ለአባቱ መጥፎ ወሬ ይዞለት መጣ። 3 እስራኤል ዮሴፍን በስተርጅናው ስለወለደው፣ ከልጆቹ ሁሉ አብልጦ ይወደው ነበር፣ በኅብረ ቀለማት ያጌጠ እጀ ጠባብም ሰፋለት። 4 ወንድሞቹም አባታቸው ከእነርሱ አብልጦ የሚወደው መሆኑን ሲያዩ ዮሴፍን ጠሉት፤ በቅን አንደበት ሊያናግሩት አልቻሉም።

5 ዮሴፍ ሕልም አለመ፤ ሕልሙንም ለወንድሞቹ ሲነግራቸው የባሰ ጠሉት፤ 6 እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ያየሁትን ሕልም ልንገራችሁ አድምጡኝ” 7 ‘እኛ ሁላችን በእርሻ ውስጥ ነዶ እናስር ነበር፤ የእኔ ነዶ ተነሣና ቀጥ ብሎ ቆመ፤ የእናንተ ነዶዎች ዙሪያውን ተሰብስበው ለእኔ ነዶ ሰገዱለት’” 8 ወንድሞቹም፣ “ታዲያ በእኛ ላይ ንጉሥ ሆነህ ልትገዛን ታስባለህን?” ብለው ጠየቁት። ስለ ሕልሙና ስለተናገረው ቃል ከፊት ይልቅ ጠሉት። 9 እንደ ገናም ሌላ ሕልም አለመ፤ ለወንድሞቹም እነሆ፣ ሌላ ሕልም አለምሁ፣ ፀሐይና ጨረቃ፣ ዐሥራ አንድ ክዋክብትም ሲሰግዱልኝ ዐየሁ” ብሎ ነገራቸው። 10 ይህንኑ ለወንድሞቹ የነገራቸውን ሕልም ለአባቱም በነገረው ጊዜ፣ አባቱ፣ “ይህ ምን ዐይነት ሕልም ነው? እኔና እናትህ ወንድሞችህም በፊትህ ወደ ምድር ተጎንብሰን በርግጥ ልንሰግድልህ ነው?” ሲል ገሠጸው። 11 ወንድሞቹ ቀኑበት፤ አባቱ ግን ነገሩን በልቡ ያዘው።

12 አንድ ቀን የዮሴፍ ወንድሞች የአባታቸውን መንጋዎች ይዘው ወደ ሴኬም ተሰማሩ፤ 13 እስራኤልም ዮሴፍን፣ “እንደምታውቀው ወንድሞችህ መንጎቹን በሴኬም አካባቢ አሰማርተዋል፤ በል ተነሥ፣ ወደ እነርሱ ልላክህ” አለው። ዮሴፍም፣ “እሺ እሄዳለሁ” አለ። 14 አባቱም፣ “በል እንግዲህ ሄድና የወንድሞችህንና የመንጋዎቹን ደኅንነት አይተህ ንገረኝ” አለው። በዚህ ዓይነት እስራኤል ዮሴፍን ከኬብሮን ሸለቆ ላከው። ዮሴፍም ሴኬም በደረሰ ጊዜ፣ 15 ሜዳ ላይ ወዲያ ወዲህ ሲባዝን አንድ ሰው አግኝቶት፣ “ምን እየፈለግህ ነው?” ሲል ጠየቀው። 16 ዮሴፍም፣ “ወንድሞቼን እየፈለግኋቸው ነው፤ መንጎቻቸውን የት እንዳሰማሩ ልትነግረኝ ትችላለህ?” አለው። 17 ሰውዬውም፣ “ከዚህ ሄደዋል፤ ደግሞም ‘ወደ ዶታይን እንሂድ’ ሲሉ ሰምቻቸዋለሁ” አለው። ከዚያም ዮሴፍ ወንድሞቹን ፍለጋ ሄደ፣ በዶታይን አቅራቢያም አገኛቸው።

18 ወንድሞቹም ዮሴፍ ወደ እነርሱ ሲመጣ በሩቅ ዐዩት፣ ወደ ነበሩበትም ስፍራ ከመድረሱ በፊት ሊገድሉት ተማከሩ። 19 እነርሱ እንዲህ ተባባሉ፦ “ያ ሕልም አላሚ መጣ፤ 20 ኑ እንግደለውና ከጉድጓዶቹ በአንዱ ውስጥ እንጣለው፤ ከዚያም፣ ‘ክፉ አውሬ ነጥቆ በላው’ እንላለን፤ እስቲ ሕልሞቹ ሲፈጸሙ እናያለን።” 21 ሮቤል ግን ይህን ምክር ሲሰማ ከእጃቸው ሊያድነው ፈለገ እንዲህም አለ፤ “አንግደለው፤ 22 የሰው ደም አታፍስሱ፣ ከምትገድሉት ይልቅ በዚህ በበረሃ ባለው ጉድጓድ ውስጥ ጣሉት” አላቸው። ሮቤል ይህን ያለው ሕይወቱን ከእጃቸው አትርፎ ወደ አባቱ ሊመልሰው ዐስቦ ነበር። 23 ዮሴፍ ወደ ወንድሞቹ እንደደረሰ፣ የለበሳትን በኅብረ ቀለማት የጌጠች እጀ ጠባቡን ገፈፉት፤ 24 ይዘውም ወደ ጉድጓድ ጣሉት፤ ጉድጓዱም ውሃ የሌለበት ደረቅ ነበር።

25 ምግባቸውን ለመብላት ተቀመጡ፤ አሻግረው ሲመለከቱም ከገለዓድ የሚመጡ እስማኤላውያን ነጋዴዎች ጓዛቸውን በግመሎች ላይ ጭነው ተመለከቱ። ነጋዴዎቹ ሽቶ፣ በለሳን፣ ከርቤ በግመሎቻቸው ጭነው ወደ ግብፅ የሚወርዱ ነበሩ። 26 ይሁዳም ወንድሞቹን እንዲህ አላቸው፤ “ወንድማችንን መግደልና አሟሟቱን መደበቅ ምን ይጠቅመናል? 27 ከዚህ ይልቅ ለእስማኤላውያን ነጋዴዎች እንሽጠው፤ እጃችንን ግን በእርሱ ላይ አናንሳ። ምንም ቢሆን የሥጋ ወንድማችን ነው” ወንድሞቹም በሃሳቡ ተስማሙ። 28 የምድያም ነጋዴዎች የሆኑ እስማሴላውያን በዚያ በኩል ያልፉ ነበር፤ ስለዚህ ወንድሞቹ ዮሴፍን ከጉድጓድ ጎትተው በማውጣት ለእነዚህ እስማኤላውያን በሃያ ብር ሸጡላቸው፣ እነርሱም ወደ ግብፅ ይዘውት ሄዱ።

29 ሮቤል ወደ ጉድጓዱ ተመልሶ ሲያይ፣ ዮሴፍን በማጣቱ ልብሱን በሐዘን ቀደደ። 30 ወደ ወንድሞቹም ተመልሶ፣ “እነሆ፣ ልጁ እዚያ የለም! እንግዲህ እኔ ወዴት ብሄድ ይሻለኛል?” አለ። 31 ከዚህ በኋላ አንድ ፍየል አረዱና የዮሴፍን ልብስ በደም ነከሩት። 32 በኅብረ ቀለማት ያጌጠችውን እጀ ጠባብ ወደ አባታቸው ወስደው፣ “ይህን ወድቆ አገኘነው፤ የልጅህ እጀ ጠባብ መሆን አለመሆኑን እስቲ እየው” አሉት። 33 እርሱ የልጁ ልብስ መሆኑን ተረድቶ፣ “ይህማ የልጄ እጀ ጠባብ ነው! ፤ ክፉ አውሬ በልቶታል፣ በእርግጥም ዮሴፍ ተቦጫጭቆአል” አለ። 34 ከዚህ በኋላ ያዕቆብ ልብሱን ቀደደ፤ ማቅም ለብሶ ስለ ልጁ ብዙ ቀን አለቀሰ፤ 35 ወንዶችና ሴቶች ልጆቹም ሁሉ ሊያጽናኑት መጡ፤ እርሱ ግን ሊጽናና አልቻለም፣ “በሐዘን እንደተኮራመትሁ ልጄ ወዳለበት መቃብር እወርዳለሁ” አለ። ስለ ልጁም አለቀሰ። 36 በዚህ ጊዜ የምድያም ነጋዴዎች ዮሴፍን ወደ ግብፅ ወስደው፣ ከፈርዖን ሹማምንት አንዱ ለነበረው ለዘበኞች አለቃ፣ ለጲጥፋራ ሸጡት።