ምዕራፍ 6

1 ወንድሞች ሆይ አንድ ሰው ስቶ ቢገኝ መንፈሳዊያን የሆናችሁ እናንት በጨዋነት መንፈስ ልታቀኑት ይገባል።ወደ ፈተና እንዳትገቡ ለራሳችሁም ተጠንቀቁ። 2 የእርስ በእርሳችሁን ሸክም በመሸካከም የክርስቶስን ህግ ፈጽሙ። 3 ምክንያቱም ማንም ምንም ሳይሆን ምንም እንደሆነ ቢያስብ ራሱን ያታልላል። 4 እያንዳንዱ ከሌላው ጋር ሳያነጻጽር የራሱን ሥራ ሊመዝን ይገባል፥ያን ጊዜ የሚመካበት ሊያገኝ ይችላል። 5 እያንዳንዱ የየራሱን ሸክም ይሸከማልና። 6 ቃሉን የሚማር ከመምህሩ ጋር ሁሉን ነገር ይካፈል ዘንድ ይገባዋል። 7 አትታለሉ እግዚአብሔር አይቀለድበትም።ሰው ምንም ነገር ቢዘራ ያንኑ ደግሞ ያጭዳል። 8 በሥጋው የሚዘራ ከሥጋው ውድቀትን ያጭዳል፤በመንፈስ የሚዘራ ግን ከመንፈስ የዘላለምን ህይወት ያጭዳል። 9 በተገቢው ጊዜ ፍሬውን እናጭዳለንና መልካምን ከመስራት አንቦዝን። 10 ስለዚህም ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ ለሰው ሁሉ በተለይም ለእምነት ቤተሰቦች መልካምን እናድርግ። 11 በገዛ እጅ ጽህፈቴ ምን ዓይነት ትልልቅ ቃላት እንደጻፍኩላችሁ ተመልከቱ። 12 እነዚያ በሥጋ መልካም መስለው የሚታዩ ስለክርስቶስ መስቀል መከራ ላለመቀበል ብለው እንድትገረዙ ያስገድዱዋችኋል።የተገረዙት እራሳቸው ህጉን አይጠብቁ፣ 13 ነገር ግን እናንተን እንድትገረዙ በማድረጋቸው ጉራ ለመንዛት እንድትገረዙ ይፈልጋሉ። 14 ዓለም ለእኔ ከተሰቀለበት እኔም ለዓለም ከተሰቀልኩበት ከክርስቶስ መስቀል በስተቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ። 15 አዲስ ፍጥረት መሆን እንጂ መገረዝም ሆነ አለመገረዝ ምንም አይጠቅምም። 16 በዚህ ሥርዓት ለሚሄዱ ሁሉ እንዲሁም የእግዚአብሔር ለሆነችው ለእስራኤል ሠላምና ምህረት ይሁን። 17 የክርስቶስን ምልክት በሥጋዬ ተሸክሜአለሁና ከእንግዲህ ማንም አይረብሸኝ። 18 ወንድሞች ሆይ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከመንፈሳችሁጋር ይሁን። አሜን!