6

1 የሰው ልጆች በምድር ላይ እየበዙ ሲሄዱ ሴቶች ልጆች ተወለዱላቸው። 2 የእግዚአብሔር ልጆችም የሰዎች ሴቶች ልጆች የሚስብ ውበት እንዳላቸው ተመለከቱ። ከእነርሱ መካከልም የመረጧቸውን ሚስቶች አድርገው ወሰዱ። 3 እግዚአብሔርም፦ “እርሱ ሥጋ ስለሆነ መንፈሴ በሰው ላይ ለዘላለም አይኖርም፤ ዕድሜውም 120 ዓመት ይሆናል” አለ። 4 የእግዚአብሔር ልጆች ከሰዎች ሴቶች ልጆች ጋብቻ በፈጸሙና ልጆችን በወለዱበት በዚያን ጊዜ ከዚያም በኋላ ኔፊሊም የተባሉ ግዙፍ ሰዎች በምድር ላይ ነበሩ። እነርሱም በጥንት ዘመን ዝናን ያተረፉ ኅያላን ነበሩ። 5 እግዚአብሔር የሰው ልጆች ክፋት በምድር ላይ እየበዛ እንደሆነና የልቡም ሃሳብ ዘወትር ወደ ክፋት ብቻ ያዘነበለ መሆኑን ተመለከተ። 6 እግዚአብሔር የሰው ልጆችን በምድር ላይ በመፍጠሩ ተጸጸተ ልቡም አዘነ። 7 በዚህም ምክንያት እግዚአብሔር፦ “የፈጠርሁትን የሰው ልጅ ከምድር ገጽ አጠፋለሁ፤ ስለፈጠርኋቸው ተጸጽቻለሁና ከእነርሱም ጋር እንስሳትን፣ በደረታቸው የሚሳቡትን ፍጥረታትና የሰማይ ወፎችን ሁሉ አጠፋለሁ” አለ። 8 ኖኅ ግን በእግዚአብሔር ዘንድ ሞገስ አገኘ። 9 የኖኅ ታሪክ እንደሚከተለው ነው። ኖኅ በዘመኑ ከነበሩት ሰዎች ሁሉ ይልቅ ጻድቅና ከበደል የራቀ ሰው ነበር፤ የእግዚአብሔርንም መንገድ የሚከተል ሰው ነበር። 10 ኖኅ ሴም፣ ካምና ያፌት የተባሉትን ሶስት ወንዶች ልጆች ወለደ። 11 በእግዚአብሔር ፊት በክፉ ሥራ ረከሰች በዓመፅም ተሞላች። 12 እግዚአብሔር ምድርን ተመለከተ፣ የተበላሸች እንደሆነችና በምድር የሚኖሩትም ሰዎች ሁሉ በክፋት እንደሚኖሩ አየ። 13 እግዚአብሔርም ኖኅን፦ “ሥጋን የለበሰ ሁሉ ፍጻሜ ደርሶአል፣ ከእነርሱ የተነሳ ምድር በግፍ ተሞልታለችና። እኔም በእርግጥ ከምድር ጋር አጠፋቸዋለሁ። 14 አንተ ግን ከጥሩ እንጨት መርከብ ሥራ፤ መርከቧም ክፍሎች እንዲኖራት አድርግ፤ ውስጧንና ውጭዋንም በቅጥራን ለቅልቀው። 15 እንደዚህ አድርገህ ሥራት፦ ርዝመቷ 140 ሜትር፣ ወርዷ 23 ሜትር፣ ከፍታዋ 13. 5 ሜትር ይሁን። 16 ለመርከቧ ጣራ አብጅላት፣ ጣራና ግድግዳው በሚጋጠምበት ቦታ ግማሽ ሜትር ክፍተት ተው፤ ከጎኗ በር አውጣላት፤ ባለ ሦስት ፎቅ አድርገህ ሥራት። 17 እኔም ከሰማይ በታች የሕይወት እስትንፋስ ያለባችውን ፍጡራን ሁሉ ለማጥፋት እነሆ በምድር ላይ የጥፋት ውሃ አወርዳለሁ፤ በምድር ላይ ያለ ሁሉ ይጠፋል። 18 ከአንተ ጋር ግን ቃል ኪዳን እገባለሁ፤ አንተና ሚስትህ፣ ልጆችህና የልጆችህ ሚስቶች ከአንተ ጋር ወደ መርከቧ ትገባላችሁ። 19 ከአንተ ጋር በሕይወት እንዲቆዩ ከሕያዋን ፍጡራን ሁሉ ወንድና ሴት እያደረግህ ሁለት ሁለቱን ወደ መርከቧ ታስገባለህ። 20 ከእያንዳንዱ የወፍ ወገን፣ ከእያንዳንዱ የእንስሳ ወገን፣ በምድር ላይ ከሚሳቡ ፍጥረት ሁሉ በየወገናቸው በሕይወት ይቆዩ ዘንድ ወደ አንተ ይምጡ። 21 ለአንተና ለእነዚህ ፍጥረቶች ሁሉ የሚበቃ ልዩ ልዩ ዓይነት ምግብ በመርከቡ ውስጥ አከማች።” 22 ኖኅም እግዚአብሔር ያዘዘውን ሁሉ አደረገ።