50

1 ዮሴፍ እጅግ ከማዘኑ የተነሣ በአባቱ ፊት ተደፍቶ አለቀሰ ሳመውም። 2 ከዚያም የአባቱ የእስራኤል አስከሬን እንዳይፈርስ ባለ መድኃኒት የሆኑ አገለጋዮች በመድኃኒት እንዲያሹት አዘዘ። ባለ መድኃኒቶቹም አስከሬኑ እንዳይፈርስ በመድኃኒት አሹት። 3 በአገሩ ልማድ መሠረት አስከሬኑ እንዳይፈርስ ማሸቱ አርባ ቀን ወሰደባቸው፤ ገብፃውያንም ሰባ ቀን አለቀሱለት። 4 የለቅሶው ወራት በተፈጸመ ጊዜ ዮሴፍ የፈርዖንን ባለሥልጣኖች እንዲህ አላቸው፤ “መልካም ፈቃዳችሁ ቢሆን እባካችሁ ለፈርዖን፣ 5 ‘አባቴ ለመሞት ሲቃረብ በከነዓን ምድር ባዘጋጀው መቃብር እንድቀብረው በመሐላ ቃል አስገብቶኛል፤ ስለዚህ ወደዚያ ሄጄ አባቴን ቀብሬ እንድመለስ ይፈቀድልኝ ሲል ጠይቆአል’ ብላችሁ ንገሩልኝ” አላቸው። 6 ፈርዖንም፣ “ባስማለህ መሠረት ሄደህ አባትህን ቅበር” አለው። 7 ስለዚህ ዮሴፍ አባቱን ለመቅበር ሄደ፣ የፈርዖን ሹማምንት በሙሉ፣ የቤተ መንግሥቱ ከፍተኛ ባለሥልጣኖች እንዲሁም የግብፅ ከፍተኛ ባለ ሥልጣኖች ሁሉ ተከተሉት። 8 እንደዚሁም የዮሴፍ ቤተ ሰቦች ወንድሞቹና ሌሎችም የአባቱ ቤተ ሰቦች ሁሉ ከዮሴር ጋር ሄዱ፣ በጌሤም የቀሩት ሕፃናት ልጆቻቸው፣ የበግ፣ የፍየልና የከብት መንጋዎቻቸው ብቻ ነበሩ። 9 እንዲሁም ሠረገሎች፣ ፈረሰኞች አብረውት ወጡ፤ አጀቡም እጅግ ብዙ ነበር። 10 እነርሱም በዮርዳኖስ ማዶ ካለው አጣድ ከተባለው ዐውድማ ሲደርሱ ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ ምርር ብለው አለቀሱ፤ ዮሴፍም በዚያ ለአባቱ ሰባት ቀን ለቅሶ ተቀመጠ። 11 በዚያ የሚኖሩ ከነዓናውያን በአጣድ ዐውድማ የተደረገውን ልቅሶ ባዩ ጊዜ፣ “ይህ ለግብፃውያን መራራ ልቅሶአቸው ነው” አሉ። በዮርዳኖስ አጠገብ ያለው የዚያ ቦታ ስም አቤል ምጽራይም ተብሎ መጠራቱም ከዚሁ የተነሣ ነበር። 12 በዚህ ሁኔታ የያዕቆብ ልጆች አባታቸው እንዳዘዛቸው አደረጉ፤ 13 አስከሬኑን ወደ ከነዓን ወስደው ከመምሬ በስተምሥራቅ በምትገኘው በማክፌላ ዋሻ ቀበሩት፤ ይህም ዋሻ አብርሃም ለመቃብር ቦት እንዲሆን ከኬጢያዊው ከኤፍሮን በገዛው እርሻ ውስጥ የሚገኝ ነው። 14 ዮሴፍ አባቱን ከቀበረ በኋላ ከወንድሞቹና ለቀብር አጅበውት ከሄዱት ሰዎች ሁሉ ጋር ሆኖ ወደ ግብፅ ተመለሰ። 15 የዮሴፍ ወንድሞች ከአባታቸው ሞት በኋላ፣ “ከፈጸምንበት በደል የተነሣ ዮሴፍ ቂም ይዞ በበቀልን ምን እናደርጋለን ተባባሉ። 16 ስለዚህ እንዲህ የሚል መልእክት ላኩ፣ አባትህ ከመሞቱ በፊት፣ 17 ‘ለዮሴፍ ወንድሞችህ በአንተ ላይ የፈጸሙትን ኃጢአትና ክፉ በደል ይቅር በላቸው’ ብላችሁ ንገሩት የሚል ትእዛዝ አስተላልፎ ነበር። አሁንም የአባትህን አምላክ አገልጋዮች ኃጢአት ይቅር በለን።” ዮሴፍ ይህን በሰማ ጊዜ አለቀሰ። 18 ከዚያም ወንድሞቹ መጡና በፊቱ ተደፍተው፣ “እኛ የአንተ አገልጋዮች ነን” አሉት። 19 ዮሴፍ ግን እንዲህ አላቸው፤ “አትፍሩ፣ እኔ በእግዚአብሔር ምትክ የተቀመጥሁ አይደለሁም፣ 20 እናንተ እኔን ለመጉዳት አስባችሁ አድርጋችሁት ነበር፤ እግዚአብሔር ግን ዛሬ እንደሚታየው ሁሉ የብዙዎችን ሕይወት ለማዳን ለበጎ ነገር አዋለው። 21 አሁንም ቢሆን አትፍሩ፤ ለእናንተና ለልጆቻችሁ የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ አደርግላችኋለሁ” በማለት በመልካም ንግግር አረጋጋቸው። 22 ዮሴፍ ከአባቱ ቤተ ሰቦች ጋር በግብፅ ተቀመጠ፤ አንድ መቶ ዐሥር ዓመትም ኖረ፤ 23 የኤፍሬምንም የልጅ ልጆች እስከ ሦስት ትውልድ ድረስ ዐየ። ከምናሴ የተወለደውንም የማኪርንም ልጆች በጭኑ ላይ አድርጎ አቀፋቸው። 24 ከዚህ በኋላ ዮሴፍ ወንድሞቹን እንዲህ አላቸው፤ “እነሆ፣ እኔ የምሞትበት ጊዜ ተቃርቦአል፤ እናንተ ግን እግዚአብሔር በረድኤት ይጎበኛችኋል፤ ከዚህም አገር አውጥቶ ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለያዕቆብ ለመስጠት በመሐላ ቃል ወደገባላቸው ምድር ይመልሳችኋል። 25 እግዚአብሔር በሚጎበኛችሁና ወደዚያች ምድር በሚመልሳችሁ ጊዜ ዐጽሜን ከዚህ ይዛችሁ የምትወጡ መሆናችሁን በማረጋገጥ ቃል ግቡልኝ” ብሎ አስማላቸው። 26 ዮሴፍም ዕድሜው መቶ ዐሥር ዓመት ሲሞላው ሞተ፣ አስከሬኑንም መድኃኒት ቀብተው በሬሳ ሳጥን ካስገቡት በኋላ በግብፅ ምድር አስቀመጡት።