47

1 ዮሴፍም ወደ ፈርዖን ሄዶ፣ “አባቴና ወንድሞቼ በጎቻቸውን፣ ፍየሎቻቸውን እንዲሁም ያላቸውን ሁሉ ይዘው ከከነዓን አገር መጥተው በጌሤም ሰፍረዋል” አለው። 2 ከወንድሞቹም መካከል አምስቱን መርጦ፣ ፈርዖን ፊት አቀረባቸው። 3 ፈርዖን የዮሴፍን ወንድሞች፣ “ሥራችሁን ምንድነው?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም ፈርዖንን፣ “እኛ አገልጋዮችህ ልክ እንደአባቶቻችን ከብት አርቢዎች ነን” አሉት። 4 ደግሞም፣ “በከነዓን ምድር ራቡ እጅግ የጸና በመሆኑ በጎችና ፍየሎች የሚሰማሩበት በማጣታቸው፣ ለጊዜው እዚህ ለመኖር መጥተናል፤ አሁንም ባሮችህ በጌሤም ምድር እንድንኖር እንድትፈቅድልን እንለምንሃለን” አሉት። 5 ፈርዖንም ዮሴፍን እንዲህ አለው፤ “አባትንህና ወንድሞችህ ወደ አንተ መጥተዋል፤ 6 የግብፅ ምድር እንደሆነ በእጅህ ነው፤ አባትህንና ወንድሞችህን ምርጥ በሆነው ምድር አስፍራቸው፤ በጌሤም ይኑሩ። ከመካከላቸው ልዩ ችሎታ ያላቸው መኖራቸውን የምታውቅ ከሆነ፣ የከብቶቼ ኅላፊዎች አድርጋቸው።” 7 ከዚህ በኋላ ዮሴፍ አባቱን ያዕቆብን ቤተ መንግሥት አግብቶ በፈርዖን ፊት አቀረበው፤ ያዕቆብ ፈርዖንን ከመረቀው በኋላ 8 ፈርዖን፣ “ለመሆኑ ዕድሜህ ምን ያህል ነው?” ሲል ያዕቆብን ጠየቀው። 9 ያዕቆብም ለፈርዖን፣ “በምድር ላይ በእንግድነት ያሳለፍሁት ዘመን 130 ዓመት ነው፤ ይህም አባቶቼ በእንግድነት ከኖሩበት ዘመን ጋር ሲነጻጸር አጭር ነው፤ ችግር የበዛበትም ነበር” ሲል መለሰለት። 10 ከዚያም ያዕቆብ ፈርዖንን መርቆ፣ ተሰናብቶት ወጣ። 11 ዮሴፍም አባቱንና ወንድሞቹን በግብፅ እንዲኖሩ አደረገ፤ ፈርዖን በሰጠውም ትእዛዝ መሠረት ምርጥ ከሆነው ምድር ራምሴን በርስትነት ሰጣቸው። 12 ዮሴፍም ለአባቱ፣ ለወንድሞቹና ለመላው የአባቱ ቤተ ሰዎች በልጆቻቸው ቁጥር ልክ ቀለብ እንዲሰፈርላቸው አደረገ። 13 በመላው ምድር እህል ባለመኖሩ ራቡ እየጸና ሄደ፤ ከዚህ የተነሣም ግብፅና ከነዓን በራብ እጅግ ተጎዱ፤ 14 ዮሴፍ የግብፅና የከነዓን ሰዎች እህል በመሸመት የከፈሉትን ገንዘብ ሁሉ ሰብስቦ ወደ ፈርዖን ቤተ መንግሥት አስገባ። 15 የግብፅና የከነዓን ሕዝቦችም ገንዘባቸው ባለቀ ጊዜ፣ ግብፃውያን ሁሉ ወደ ዮሴፍ ቀርበው፣ “የምንበላው እህል ስጠን፣ ገንዘባችን አልቆብናል፤ ዓይንህ እያየ እንዴት በራብ እንለቅ?” አሉት። 16 ዮሴፍም ከብቶቻችሁን አምጡ፣ ገንዘባችሁ ካለቀ በከብቶቻችህ ለውጥ እህል እሰጣችኋለሁ አለ። 17 ስለዚህ ከብቶቻቸውን ወደ ዮሴፍ አምጡ፤ እርሱም በፈረሶቻቸው፣ በበጎቻቸው፣ በፍየሎቻቸው፣ በከብቶቻቸውና በአህዮቻቸው ለውጥ እህል ሰጣቸው። በከብቶቻቸው ልዋጭ ባገኙት ምግብ በዚያ ዓመት ሳይራቡ እንዲያልፉ አደረጋቸው። 18 ያም ዓመት ካለፈ በኋላ ሕዝቡ በሚቀጥለው ዓመት ወደ ዮሴፍ መጥተው እንዲህ አሉት፣ “እንግዲህ ከጌታችን የምንሰውረው ምንም ነገር የለም፤ ገንዘባችን አልቆአል፤ ከብቶቻችንንም አስረክበንሃል፤ እንግዲህ ለጌታችን የምንሰጠው፣ ከሰውነታችንና ከመሬታችን በቀር ሌላ ምንም ነገር የለንም። 19 ታዲያ እያየኸን እንዴት እንለቅ? መሬታችንም ለምን ጠፍ ሆኖ ይቅር? እኛንና መሬታችንን ውሰድና በለውጡ እህል ስጠን፤ እኛ የፈርዓን አገልጋዮች እንሆናለን፤ መሬታችንም የእርሱ ይሁን፣ እኛም እንዳንሞት መሬታችንም ጠፍ ሆኖ እንዳይቀር የምንዘራው ዘር ስጠን። 20 ስለዚህ ዮሴፍ የግብፅን ምድር ሁሉ ለፈርዖን ገዛለት፤ ራቡም እጅግ ስለጸናባቸው ግብፃውያን ሁሉ መሬታቸውን ሸጡ፣ ምድሪቱም የፈርዖን ርስት ሆነች። 21 ዮሴፍ በግብፅ አገር ዳር እስከ ዳር ያሉት ሰዎች ሁሉ የንጉሡ አገልጋዮች እንዲሆኑ አደረገ። 22 ሆኖም ዮሴፍ የካህናቱን መሬት አልገዛም፤ ምክንያቱም ካህናቱ ከፈርዖን ቋሚ አበል ስለሚያገኙ እርሱም ከሚሰጣቸው አበል ምግብ ያገኙ ስለነበረ መሬታቸውን አልሸጡም። 23 ዮሴፍ ሕዝቡን እንዲህ አላቸው፣ “እነሆ፣ ዛሬ እናንተንም መሬታችሁንም ለፈርዖን ገዝቻችኋለሁና ይህን ዘር ወስዳችሁ በመሬት ላይ ዝሩ። 24 መከሩ በሚሰበሰብበት ጊዜ ግን ከአምስት እጅ አንዱን ለፈርዖን ታስገባላችሁ፣ ከአምስት እጅ አራቱን ደግሞ ለመሬታችሁ ዘር፣ እንዲሁም ለራሳችሁ፣ ለቤተ ሰቦቻችሁና ለልጆቻችሁ ምግብ ታደርጉታላችሁ።” 25 እነርሱም፣ “እንግዲህ ሕይወታችንን አትርፈህልናል፤ በጌታችን ፊት ሞገስ ካገኘን ለፈርዖን ገባሮች እንሆናለን” አሉት። 26 ስለዚህ ዮሴፍ የምርቱ አንድ አምስተኛ ለፈርዖን እንዲገባ የሚያዝ የመሬት ሕግ አወጣ፤ ይህም ሕግ እስከ ዛሬ ይሠራበታል። በፈርዖን እጅ ያልገባው መሬት የካህናቱ ብቻ ነው። 27 በዚህ ጊዜ እስራኤላውያን በግብፅ አገር በጌሤም ይኖሩ ነበር፣ በዚያም ሀብት ንብረት አፈሩ፤ ቁጥራቸውም እጅግ እየበዛ ይሄድ ጀመር። 28 ያዕቆብ በግብፅ ዐሥራ ሰባት ዓመት ኖረ፣ ዕድሜውም አንድ መቶ አርባ ሰባት ዓመት ነበር። 29 እስራኤልም የሚሞትበት ጊዜ መቃረቡን እንደተረዳ ልጁን ዮሴፍን አስጠርቶ እንዲህ አለው፤ “በአንተ ዘንድ ሞገስ ካገኘሁ እጅህን በጭኔ ላይ አኑረህ፣ በጎነትንና ታማኝነትን ልታደርግልኝ ቃል ግባልኝ፤ በምሞትበት ጊዜ በግብፅ አትቅበረኝ፤ 30 እኔም ከአባቶቼ ጋር ሳንቀላፋ ከግብፅ አውጥተህ እነርሱ በተቀበሩበት ቦት ቅበረኝ” ዮሴፍም፣ “እሺ፣ እንዳልኸኝ አደርጋለሁ” አለ። 31 ያዕቆብ፤ “በል ማልልኝ” አለው። ዮሴፍም ማለለት፣ እስራኤልም በአልጋው ራስጌ ላይ ሆኖ ጎንበስ አለ።