38

1 በዚያም ወራት ይሁዳ ከወንድሞቹ ተለይቶ ሒራ ወደተባለ ዐዱላማዊ ሰው ዘንድ ሄደ፣ መኖሪያውንም 2 እዚያም ሳለ፣ ይሁዳ የከነዓናዊውን የሴዋን ሴት ልጅ ዐየ፤ እርሷንም አግብቶ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ፈጸመ። 3 እርሷም አርግዛ ወንድ ልጅ ወለደችለት፤ ስሙንም ዔር ብላ ጠራችው። 4 እንደገናም አረገዘችና ወንድ ልጅ ወለደችለት፤ ስሙንም አውናን አለችው። 5 አሁንም ደግማ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ስሙንም ሴሎም ብላ ጠራችው፣ እርሱንም የወለደችው ክዚብ በተባለ ቦታ ነበር። 6 ይሁዳ የመጀመሪያ ልጁን ዔርን ትዕማር ከምትባል ልጃገረድ ጋር አጋባው። 7 የይሁዳ የበኩር ልጅ ዔር ግን በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነበር፤ እግዚአብሔርም ቀሠፈው። 8 ይሁዳ አውናንን፣ “ዋርሳዋ እንደመሆንህ ከወንድምህ ሚስት ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት በመፈጸም የወንድምህን ስም የሚያስጠራለት ዘር ተካለት አለው። 9 አውናን ግን የሚወለደው ልጅ የእርሱን ስም የሚያስጠራ እንደማይሆን ስላወቀ፣ ከወንድሙ ሚስት ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት በፈጸመ ቁጥር የወንድሙን ስም የሚያስጠራ ልጅ እንዳይወለድ ዘሩን በምድር ላይ ያፈስ ነበር። 10 ይህም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሆኖ ስለተገኘ፣ እርሱንም እግዚአብሔር በሞት ቀሠፈው። 11 ከዚያም ይሁዳ ምራቱን ትዕማርን፣ “ልጄ ሴሎም ለአካለ መጠን እስኪደርስ ድረስ ወደ አባትሽ ቤት ሄደሽ መበለት ሆነሽ ብትኖሪ ይሻላል” አላት፤ ይህን ያለውም፤ ሴሎም እንደወንድሞቹ ተቀሥፎ ይሞትብኛል ብሎ ስለፈራ ነበር። ትዕማርም እንዳላት ሄደች፤ በአባቷም ቤት ተቀመጠች። 12 ከብዙ ጊዜ በኋላ የሹዓ ልጅ፣ የይሁዳ ሚስት ሞተች። ይሁዳ ከሐዘኑ ከተጽናና በኋላ ከዓዶላማዊው ከሒራ ጋር የበጎቹን ጠጉር የሚሸልቱ ሰዎች ወዳሉበት ወደተምና ሄደ። 13 ሰዎቹም ለትዕማር፣ “አማትሽ የበጎቹን ጠጉር ወደሚሸልቱ ሰዎች ዘንድ ወደተምና እየሄዱ ነው” አሏት። ይህን እንድሰማች 14 የመበለትነት ልብሷን አውልቃ፣ ማንነቷ እንዳይታወቅ ፊቷን በሻሽ ተከናንባ ወደ ተምና በሚወስደው መንገድ ዳር ባለች ኤናይም በተባለች ከተማ መግቢያ በር ላይ ተቀመጠች፤ ይህን ያደረገችው፣ ሴሎም ለአካለ መጠን ቢደርስም፣ እርሷን እንዲያገባ አባቱ አለመፈለጉን ስላወቀች ነው። 15 ፊቷ በሻሽ ተሸፋፍኖ ሲያያት፣ ይሁዳ ዝሙት አዳሪ መሰለችው። 16 ምራቱ መሆኗን ባለማወቁ፣ እርሷ ወዳለችበት ወደ መንደሩ ዳር ጠጋ ብሎ፣ “እባክሽን አብሬሽ ልተኛ” አላት። እርሷም፣ “አብሬህ ብተኛ ምን ትሰጠኛለህ?” ብላ ጠየቀችው። 17 “ከመንጋዬ መካከል አንድ የፍየል ጠቦት እልክልሻለሁ” አላት። እርሷም “ጠቦቱን እስክትልክልኝ ድረስ ምን መያዣ ትሰጠኛለህ?” ብላ ጠየቀችው። 18 “ታዲያ ምን መያዣ ልስጥሽ?” አላት። እርሷም፣ “የማኅተም ቀለበትህን ከነማሰሪያው፣ እንደዚሁም ይህን በትርህን ስጠኝ” አለችው። የጠየቀችውን ሁሉ ሰጣትና አብሯት ተኛ፤ እርሷም አረገዘችለት። 19 ከዚያም ወደ መኖሪያዋ ተመልሳ፣ ሻሽዋን አውልቃ እንደወትሮዋ የመበለት ለብሷን ለበሰች። 20 ይሁዳ በመያዣ ስም የሰጣትን ዕቃዎች ለማስመለስ የፍየሉን ጠቦት በዓዶሎማዊ ወዳጁ እጅ ላከላት፣ እርሱ ግን ሊያገኛት አልቻለም። 21 “በኤናይም ከተማ መግቢያ ከመንገዱ ዳር የነበረች ያቺ ዝሙት አዳሪ የት ደረሰች?” ብሎ ዓዶሎማዊው ሰውዬ ጠየቀ። ሰዎቹም፣ “በዚህ አካባቢ እንደዚህ ያለች ዝሙት አዳሪ የለችም” አሉት። 22 ስለዚህ ወደ ይሁዳ ተመልሶ ሄደና፣ “ላገኛት አልቻልሁም፤ በዚያ የሚኖሩትም ሰዎች፥ ‘እንደዚህ ያለች ዝሙት አዳሪ እዚህ የለችም’ አሉኝ” ብሎ ነገረው። 23 ይሁዳም፣ “እንግዲህ መያዣውን እንደያዘች ትቅር አለዚያ መሳቂያ እንሆናለን። ለነገሩማ ይህን ፍየል ላክሁ፣ አንተም ፈልገህ አላገኘሃትም” አለ። 24 ከሦስት ወር ያህል በኋላ፣ “ምራትህ ትዕማር ዘማዊ ሆናለች፤ ከዚህም የተነሣ አርግዛለች” ተብሎ ለይሁዳ ተነገረው። ይሁዳም፣ “አውጧትና በእሳት ተቃጥላ ትሙት” አለ። 25 እርሷም ተይዛ በምትወሰድበት ጊዜ ለአማትዋ፣ “እኔ ያረገዝሁት የእነዚህ ዕቃዎች ባለቤት ከሆነ ሰው ነው” ስትል ላከችበት፤ ደግሞም፣ “የማኅተሙ ቀለበት ከነማንጠልጠያውና በትሩ የማን እንደሆነ እስቲ ተመልከት” አለችው። 26 ይሁዳም ዕቃዎቹን አውቆ፣ “ልጄ ሴሎም እንዲያገባት ባለማድረጌ፣ እርሷ ከእኔ ይልቅ ትክክል ናት” አለ። ከዚያም በኋላ ከእርሷ ጋር አልተኛም። 27 የመውለጃዋ ጊዜ እንደደረሰም ፅንሷ መንታ መሆኑ ታወቀ። 28 በምትወልድበትም ጊዜ አንደኛው እጁን አወጣ፤ አዋላጂቱም፣ “ይህኛው መጀመሪያ ወጣ” ስትል በእጁ ላይ ቀይ ክር አሰረችለት፤ 29 ነገር ግን፣ እጁን መልሶ ሲያስገባ ወንድሙ ተወለደ። አዋላጂቱም፣ “አንተ እንዴት ጥሰህ ወጣህ!” አለች፣ ከዚያም ስሙ ፋሬስ ተባለ። 30 ከዚያ በኋላ እጁ ላይ ቀይ ክር የታሰረለት ወንድሙ ተወለደ፣ ስሙም ዛራ ተባለ።