35

1 እግዚአብሔር ያዕቆብን፣ “ተነሣና ወደ ቤቴል ሂድ፣ እዚያም ኑር። ከወንድምህ ከዔሳው ሸሽተህ በሄድህ ጊዜ ለተገለጠልህ አምላክ በዚያ መሠዊያ ሥራ አለው። 2 ስለዚህም ያዕቆብ ለቤቱ ሰዎችና አብረውት ለነበሩት ሁሉ እንዲህ አላቸው፤ “በእናንተ ዘንድ ያሉትን ባዕዳን አማልክት አስወግዱ፤ ሰውነታችሁን አንጹ፤ ልብሳችሁንም ለውጡ። 3 ተነሥተን ወደ ቤቴል እንሂድ፤ እዚያም በመከራዬ ጊዜ ለሰማኝ በሄድሁበትም ስፍራ ሁሉ ላልተለየኝ አምላክ መሠዊያ እሠራለሁ። 4 ስለዚህ በእነርሱ ዘንድ የነበሩትን ባዕዳን አማልክት ሰብስበው፣ የጆሮ ጉትቾቻቸውን አውልቀው ለያዕቆብ ሰጡት። ያዕቆብም ወስዶ ሴኬም አጠገብ ካለው ዋርካ ዛፍ ሥር ቀበራቸው። 5 ያንንም ቦታ ለቀው ሄዱ፤ እግዚአብሔርም በዙሪያቸው በነበሩት ከተሞች ሁሉ ላይ ፍርሃትና ድንጋጤ ስለለቀቀባቸው ያሳደዳቸው አልነበረም። 6 ያዕቆብና አብረውት የነበሩት ሰዎች ሁሉ በከነዓን ወደምትገኘው፣ ቤቴል ወደተባለችው ወደ ሎዛ ደረሱ። 7 ያዕቆብም በዚያ ስፍራ መሠዊያ ሠርቶ፣ ስሙን ኤል ቤቴል አለው፤ ምክንያቱም ከወንድሙ ሸሽቶ በሄደ ጊዜ እግዚአብሔር የተገለጠለት በዚህ ቦታ ነበር። 8 በዚህ ጊዜ የርብቃ ሞግዚት ዲቦራ ሞተች፣ ከቤቴል ዝቅ ብሎ በሚገኘው የዋርካ ዛፍ ሥር ተቀበረች። ከዚህ የተነሣም ያ ቦታ አሉንባኩት ተባለ። 9 ያዕቆብ ከመስጴጦምያ በተመለሰ ጊዜ እግዚአብሔር ዳግመኛ ተገለጠለትና ባረከው። 10 እግዚአብሔርም፣ “እስካሁን ስምህ ያዕቆብ ነበር፤ ከእንግዲህ ያዕቆብ ተብለህ አትጠራም፤ ነገር ግን ስምህ እስራኤል ይባላል” አለው። ስለዚህም እስራኤል ብሎ ጠራው። 11 ደግሞም እግዚአብሔር ያዕቆብን እንዲህ አለው፤ “እኔ ሁሉም ማድረግ የሚችል አምላክ ነኝ፤ ብዙ ልጆች ይኑሩህ፤ ዘርህም ይብዛ፤ የብዙ ሕዝብ አባት ሁን፤ ነገሥታትም ከአንተ ይወለዱ። 12 ለአብርሃምና ለይስሐቅ የሰጠኋትን ምድር ለአንተ እሰጣለሁ፤ ከአንተም በኋላ ይህችን ምድር ለዘርህ አሰጣለሁ።” 13 እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከተነጋገረ በኋላ ከዚያ ስፍራ ወደ ላይ ወጣ። 14 ያዕቆብ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር በተነጋገረበት ስፍራ የድንጋይ ሐውልት አቆመ፣ በሐውልቱ ላይ የመጠጥ ቁርባን አፈሰሰ፤ ዘይትም አፈሰሰበት። 15 ያዕቆብም እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር የተነጋገረበትን ስፍራ ቤቴል ብሎ ጠራው። 16 ከዚያም ከቤቴል ተነሥተው ሄዱ፤ ኤፍራታ ለመድረስ ጥቂት ሲቀራቸው ራሔልን ምጥ ያዛት፣ ምጡም ጠናባት። 17 ምጧ እየበረታ በሄደ ጊዜ አዋላጅቱ፣ “አይዞሽ አትፍሪ፤ ሌላ ወንድ ልጅ ልትወልጂ ነው” አለቻት። 18 እርስዋ ግን ልትሞት ታጣጥር ስለነበር ከመሞቷ በፊት ልጅዋን ‘ቤንኦኒ’ አለችው፤ አባቱ ግን ‘ብንያም’ አለው። 19 ራሔል ሞተች፤ ወደ ኤፍራታ በሚወስደው መንገድ በቤተልሔም ተቀበረች። 20 ያዕቆብም በራሔል መቃብር ላይ ሐውልት አቆመ፤ እስከዛሬም የራሔል መቃብር ምልክት ይኸው ሐውልት ነው። 21 ያዕቆብ ጉዞውን ቀጥሎ በዔዴር ግንብ ባሻገር ድንኳን ተክሎ ሰፈረ። 22 ያዕቆብ በዚያ ምድር ሲኖር ሳለ፣ ሮቤል ከአባቱ ቁባት ከባላ ጋር የግብረሥጋ ግንኙነት አደረገ፤ ያዕቆብም ይህን ነገር ሰማ ያዕቆብ ዐሥራ ሁለት ወንዶች ልጆች ነበሩት፣ እነርሱም፦ 23 የልያ ልጆች፦ የያዕቆብ የበኩር ልጅ ሮቤል፣ ስምዖን፣ ሌዊ፣ ይሁዳ፣ ይሳኮር፣ ዛብሎን፤ 24 የራሔል ልጆች፦ ዮሴፍ፣ ብንያም፤ 25 የራሔል አገልጋይ የባላ ልጆች፦ ዳን፣ ንፍታሌም፤ 26 የልያ አገልጋይ የዘለፋ ልጆች፦ ጋድ፣ አሴር፣ ናቸው። እነዚህ ወንዶች ልጆች ያዕቆብ በመስጴጦምያ ሳለ የተወለዱለት ናቸው። 27 ያዕቆብ በቂርያት አርባቅ (በኬብሮን) አጠገብ መምሬ በምትባል ስፍራ ወደሚኖረው አባቱ ወደ ይስሐቅ ሄደ፤ ይህም ስፍራ አብርሃምና ይስሐቅ የኖሩበት ነው። 28 ይስሐቅ መቶ ሰማንያ ዓመት ኖረ፤ 29 አርጅቶ ዕድሜ ጠግቦ ሞተ፤ ወደ ወገኖቹ ተሰበሰበ፤ ልጆቹም ዔሳውና ያዕቆብ ቀበሩት።