22

1 ሁሉ ነገር በኋላ እግዚአብሔር አብርሃምን ፈተነው፤ እግዚአብሔርም «አብርሃም»ብሎ ጠራው፤ «እነሆ አለሁኝ» ብሎ መለሰ። 2 እግዚአብሔርም «የምትወደውን አንድ ልጅህን ወደ ሞሪያ ምድር ሂድ። እዚያ በማሳይህ አንድ ኮረብታ ላይ እርሱን የሚቃጠል መስዋዕት አድርገህ አቅርብልኝ» አለው፤ 3 አብርሃም በማለዳ ተነስቶ ለመስዋዕት የሚሆን እንጨት ቆረጠና በአህያው ላይ ጫነው፤ከእርሱ ጋር ልጁን ይስሐቅን ና ሁለት ወጣት ሰዎችን ይዞ እግዚአብሔር ወደ ነገረው ቦታ ለመሄድ ጉዞ ጀመረ። 4 በሦስተኛው ቀን አብርሃም ቀና ብሎ ሲመለከት ቦታውን በሩቅ አየ። 5 ከዚህ በኃላ አብርሃም የርሱን ወጣቶች «እናንተ ከአህያው ጋር በዚህ ቆዩ እኔና ልጄ ወደዚያ ሄደን ከሰገድን በኃላ እንመለሳለን፤ 6 አብርሃምም የሚቃጠለውን መስዋዕቱን ማቃጠያ እንጨት አንስቶ ለልጁ ለይስአቅ አሸከመው፤ እርሱ ግን ቢላዋውንና እሳቱን ያዘ ሁለቱም አብረው ሄዱ። 7 ይስሐቅ አብርሃምን «አባባ» አለው፤ እርሱም «እነሆ አለሁ ልጄ» አለው፤ ይስሐቅም «እነሆ እሳትና እንጨት ይዘናል ታዲያ ለመስዋዕት የሚሆነው በግ የት አለ?» በማለት አብርሃምን ጠየቀው። 8 አብርሃምም «ልጄ ሆይ ለመስዋዕት የሚሆነውን በግ እግዚአብሔር እራሱ ያዘጋጃል» አለው። ሁለቱም አብረው መንገዳቸውን ቀጠሉ። 9 እግዚአብሔር ነገረው ቦታ በደረሱ ጊዜ አብርሃም መሰዊያ ሰርቶ እንጨቱን ረበረበው፤ ልጁን ይስሐቅንም አስሮ ከእንጨቱ በላይ በመሰዊያው ላይ አጋደመው። 10 ልጁን ለማረድ ቢላዋ አንስቶ እጁን ዘረጋ። 11 ነገር ግን የእግዚአብሔር መልአክ ከሰማይ «አብርሃም! አብርሃም!» ብሎ ጠራው። እርሱም «እነሆኝ አለሁኝ» አለ። 12 እርሱም «በልጁ ላይ እጅህን አትጫንበት፣ ምንም ዓይነት ጉዳትም አታድርስበት፣ እነሆ እግዚአብሔርን የምትፈራ መሆንህን ተረድቻለሁ፤ አንድ ልጅህን እንኳ ለእኔ ከመስጠት አልተቆጠብህም» አለው። 13 አብርሃም ዙሪያውን በተመለከት ጊዜ ከበስተጀርባው ቀንዶቹ በቁጥቋጥ ዛፍ የተያዙ አንድ በግ አየ፤ አብርሃምም ሄዶ በጉን አመጣና በልጁ ፋንታ የሚቃጠል መስዋዕት አድርጎ አቀረበው። 14 አብርሃምም ያን ቦታ «እግዚአብሔር ያዘጋጃል» ብሎ ጠራው። ዛሬም ቢሆን ሠዎች «እግዚአብሔር በተራራው ላይ ያዘጋጃል» ይላሉ። 15 የእግዚአብሔር መልአክ ለሁለተኛ ጊዜ አብርሃምን ከሰማይ ጠራውና፤ 16 እንዲህ አለው፤ «እግዚአብሔር ብዙ በረከት እንድምሰጥህ በራሴ ስም እምላለሁ» ይላል፤ ይህን ስላደረግህና አንድ ልጅህንም ለእኔ ለመስጠት ስላልተቆጠብህ፤ 17 እኔም ዘርህን እንደ ሰማይ ከዋክብትና እንደ ባህር ዳር አሸዋ አበዛዋለሁ፤ ዝርያዎችህም ጠላቶቻቸውን ድል ነስተው፤ ከተሞቻቸውን ይይዛሉ። 18 ትዕዛዜን ስለ ፈጸምህ የዓለም ህዝቦች ሁሉ በዘርህ ይባረካሉ»፤ 19 ከዚህ በኋላ አብርሃም ወደ ወጣቶችሁ ተመለሰና በአንድነት ሆነው ወደ ቤርሳቤህ ሄዱ፤ አብርሃምም በቤርሳቤህ ተቀመጠ። 20 ከዚህ ሁሉ በኋላ እንዲህ ተብሎ ለአብርሃም ተነገረው «ሚልካ ልጆችን ለወንድምህ ለናኮር ወልዳለች፤ 21 እነርሱም የመጀመሪያው ልጅ ዑፅ ወንድሙም ቡዝ የአራም አባት ቀሙኤል፤ 22 ኬሰድ፣ ሐዞ፣ ፊልዳሽ፤ ይድላፍና በቱኤል ናቸው። 23 በቱኤል ርብቃን ወለደ። ሚልካ እነዚህን ስምንት ልጆች ለአብርሃም ወንድም ለንኮር ወለደችለት፤ 24 ረኡማ የተባለች የናኮር ቁባት ደግሞ ጤባሕን፣ ገሐምን፣ ተሐሽና ማዕካን ወለደችለት።