15

1 ከዚህ በኋላ የያህዌ ቃል እንዲህ ሲል ወደ አብራም መጣ፤ “አብራም ሆይ፣ አትፍራ፤ እኔ ለአንተ ጋሻህ ነኝ፤ ታላቅ ሽልማትህም እኔው ነን።” 2 አብራምም፣ “ጌታ ያህዌ ሆይ፣ እኔ ልጅ የለኝም፤ የቤት ወራሽ የሚሆነው የደማስቆው ሰው ኤሊዔዘር ነው፤ ታዲያ አንተ ለእኔ የምትሰጠኝ ምንድን ነው?” አለ። 3 በመቀጠልም አብራም “አንተ ልጅ እስካልሰጠኸኝ ድረስ፣ ከቤቴ አገልጋይ አንዱ ወራሼ መሆኑ አይቀርም” አለ። 4 በዚህ ጊዜ የያህዌ ቃል እንዲህ ሲል ወደ እርሱ መጣ፤ “ይህ ሰው ወራሽህ አይሆንም፤ ይልቁንም ወራሽህ የሚሆነው ከአብራክህ የሚከፈል የራስህ ልጅ ይሆናል።” 5 ከዚያም ወደ ውጭ አወጣውና እንዲህ አለው፤ “ቀና ብለህ ወደ ሰማይ ተመልከት፤ መቍጠር ከቻልህ ከዋክብቱን ቍጠር። ዘርህም እንዲሁ ይበዛል።” 6 አብራም ያህዌን አመነ፤ እርሱም ጽድቅ አድርጎ ቆጠረለት። 7 እንዲህም አለው፤ “ይህችን ምድር እንድትወርስ ልሰጥህ ከከለዳውያን ምድር ከዑር ያወጣሁህ እኔ ያህዌ ነኝ።” 8 አብራምም፣ “ጌታ ያህዌ ሆይ፣ ይህችን ምድር እንደምወርስ እንዴት አውቃለሁ?” አለ። 9 በዚህ ጊዜ፣ “እያንዳንዳቸው ሦስት ዓመት የሆናቸው አንዲት ጊደር፣ አንዲት ፍየልና አንድ በግ እንዲሁም ዋኖስና አንድ ርግብ አቅርብልኝ” አለው። 10 እርሱም እነዚህን ሁሉ አቀረበለት፤ ቆርጦም ሁለት ቦታ ከከፈላቸው በኋላ እያንዳንዱን ክፍል በሌላው ወገን ትይዩ አስቀመጣቸው፤ ወፎቹን ግን አልከፈላቸውም። 11 አሞሮች ሥጋውን ለመብላት ወረዱ፤ አብራምም አባረራቸው። 12 ፀሓይ ልትጠልቅ ስትል አብራም ከባድ እንቅልፍ ወሰደው፤ የሚያስፈራም ድቅድቅ ጨለማም መጣበት። 13 በዚህ ጊዜ ያህዌ አብራምን እንዲህ አለው፤ “ዘሮችህ የራሳቸው ባልሆነ ምድር ባዕድ እንደሚሆኑና እዚያ ለአራቶ መቶ ዓመት በባርነት እንደሚኖሩ በእርግጥ ዕወቅ። 14 እኔም ባሪያዎች ባደረጓቸው ሕዝብ እፈርዳለሁ፤ በኋላም ብዙ ሀብት ይዘው ይወጣሉ። 15 አንተ ግን በሰላም ወደ አባቶችህ ትሄዳለህ፤ ዕድሜም ጠግበህ ትቀበራለህ። 16 በአራተኛውም ትውልድ እንደ ገና ወደዚህ ይመጣሉ፤ ምክንያቱም የአሞራውያን ኀጢአት ጽዋው ገና አልሞላም።” 17 ፀሓይ ገብታ ከጨለመ በኋላ የምድጃ ጢስና የሚንበለበል ፋና በተቆራረጡት ሥጋዎች መካከል አለፈ። 18 በዚያን ቀን ያህዌ እንዲህ በማለት ከአብራም ጋር ኪዳን አደረገ፤ “ከግብፅ ወንዝ ጀምሮ እስከ ታላቁ ወንዝ ኤፍራጥስ ድረስ ያለውን ምድር ለዘርህ እሰጣለሁ፤ 19 የምሰጣቸውም የቄናውያንን፣ የቄንፌዛውያንን፣ የቃድሞናውያንን፣ 20 የኬጢያውያንን፣ የፌርዛውያንን፣ የራፋይምን፣ 21 የአሞራውያንን፣ የከነዓናውያን፣ የጌርሳውያንንና የኢያቡሳውያን ምድር ነው።”