12

1 በዚህ ጊዜ ያህዌ አብራምን እንዲህ አለው፤ “አገርህን፣ ወገንህንና የአባትህን ቤተ ሰብ ትተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ሂድ፤ 2 ታላቅ ሕዝብ አደርግሃለሁ፤ እባርክሃለሁ፤ ስምህን ገናና አደርገዋለሁ፤ ለሌሎችም በረከት አደርግሃለሁ። 3 የሚባርኩህን እባርካለሁ፤ የሚረግሙህንና የሚያዋርዱህን እረግማለሁ። በአንተ አማካይነት በምድር የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ይባረካሉ።” 4 ስለዚህ አብራም ያህዌ እንዳዘዘው ወጣ፤ ሎጥም አብሮት ሄደ። አብራም ከካራን ተነሥቶ ሲሄድ፣ የሰባ አምስት ዓመት ሰው ነበር። 5 አብራም ሚስቱ ሦራን፣ የውንድሙ ልጅ ሎጥን አስከትሎ በካራን ያፈሩትን ሀብትና የነበራቸውን አገልጋዮች ይዞ በመጓዝ፣ ከነዓን ምድር ገቡ። 6 አብራም በሞሬ ያለው ግዙፍ የወርካ ዛፍ እስካለበት እስከ ሴኬም ዘልቆ ሄደ። በዚያ ዘመን ከነሻናውያን በዚህ ምድር ይኖሩ ነበር። 7 ያህዌ ለአብራም ተገልጦ፣ “ይህችን ምድር ለዘርህ እሰጣለሁ” አለው። ስለዚህ አብራም ለተገለጠለት ለያህዌ በዚያ መሠዊያ ሠራ። 8 ከዚያ በመነሣት ከቤቴል በስተ ምሥራቅ ወዳለው ተራራማ አገር ሄደ፤ ቤቴል በስተ ምዕራብ፣ ጋይ በስተ ምዕራብ ባለችበት ቦታ ድንኳኑን ተከለ። እዚያ ለያህዌ መሠዊያ ሠራ፤ የያህዌንም ስም ጠርቶ ጸለየ። 9 አብራም ከዚያ ተነሥቶ ወደ ኔጌብ መጓዙን ቀጠለ። 10 በዚያ ምድር ጽኑ ራብ ስለ ነበር አብራም እዚያ ጥቂት ጊዜ ለመቆየት ወደ ግብፅ ሄደ። 11 ግብፅ በመግባት ላይ እያለ አብራም ሚስቱ ሦራን እንዲህ አላት፤ “መቼም አንቺ ቆንጆ ሴት መሆንሽን አውቃለሁ። 12 ግብፃውያን ሲያዩሽ ‘ይህች ሚስቱ ናት’ ይላሉ፤ እኔን ይገድሉኛል፤ አንቺን ግን ይተዉሻል። 13 ስለዚህ በአንቺ ምክንያት ለእኔ መልካም እንዲሆልኝ ሕይወቴም እንዲተርፍ እኅቱ ነኝ’ በዪ አላት። 14 አብራም ወደ ግብፅ ሲገባ፣ ሦራ ምን ያህል ቆንጆ እንደ ሆነች ግብፃውያኑ አዩ። 15 የፈርሾን ሹማምንት ባዩአት ጊዜ እርሷን እያደነቁ ለፈርዖን ነገሩት፤ ወደ ቤተ መንግሥትም ተወሰደች። 16 በእርሷ ምክንያት ፈርኦን አብራምን በክብር አስተናገደው፤ በጎች፣ በሬዎች፣ ወንድ አህዮች ወንድና ሴት ባሪያዎች፣ ሴት አህዮችና ግመሎች ሰጠው። 17 በአብራም ሚስት በሦራ ምክንያት ያህዌ ፈርዖንና ቤተ ሰቡን በታላቅ መቅሠፍት መታ። 18 ፈርዖን አብራምን አስጠርቶ እንዲህ አለው፤ “ለመሆኑ ምን እያደረግህብኝ ነው? ሚስትህ መሆንዋን ለምን አልነገርከኝም? 19 ለምን እኅቴ ናት አልከኝ? እኅቴ ናት ስላልከኝ ሚስቴ ላደርጋት ነበር። አሁንም ሚስትህ እቻት፤ ይዘሃት ሂድ” 20 ከዚያም ፈርዖን አብራምን በተመለከተ ለባለሟሎቹ ትእዛዝ ሰጠ፤ እነርሱም አብራምን ከሚስቱና ከንብረቱ ሁሉ ጋር አሰናበቱት።