27

1 ይስሐቅ አርጅቶ ዐይኖቹም ታውረው ነበር፤ ታላቁ ልጁን ዔሳውን፤ "ልጄ ሆይ!" ብሎ ጠራው፤ ልጁም "እነሆ አለሁ" አለ። 2 ይስሐቅም እንዲህ አለው፣ "እንደምታየኝ አርጅቻለሁ፤ የምሞትበትንም ቀን አላውቅም፤ 3 ስለዚህ የምታድንበትን ቀስትና ፍላጻ ያዝ፤ ወደ ዱር ሂድና አውሬ አድነህ ሥጋ አምጣልኝ፤ 4 ልክ እንደምወደው አድርገህ ምግብ ሥራልኝ ከበላሁም በኋላ ከመሞቴ በፊት የመጨረሻ ምርቃቴን እሰጥሃለሁ።"

5 ይስሐቅ ለልጁ ለዔሳው ወደ አደን ከሄደ በኋላ፣ 6 ርብቃ ልጅዋን ያዕቆብን "አባትህ ዔሳውን እንዲህ ሲለው ሰማሁ፣ 7 አውሬ አድነህ ሥጋ አምጣልኝ፤ ልክ እንደምወደው አድርገህ የጣፈጠ ምግብ ሥራልኝ፤ ሳልሞትም በእግዚአብሔር ፊት እነርቅሃለሁ፤ 8 አሁንም ልጄ ሆይ! የምነግርህን አድምጥ፤ የማዝህንም አድርግ፤ 9 አባትህ እንደሚወደው አጣፋጩ ጥሩ ምግብ እንድሠራለት፣ ወደ መንጋዎች ሂድና ሁለት የሰቡ የፍየል ጥቦቶች አምጣልኝ፤ 10 አንተም ያዘጋጀሁትን ምግብ እንዲበላ ለአባትህ ወስደህ ታቀርብለታለህ፤ በዚህ ዐይነት አባትህ ከመሞቱ በፊት ይመርቅሃል።" 11 ያዕቆብ ግን እናቱን ርብቃን "የወንድሜ የዔሳው ገላ ጠጉራም ነው፤ የ እኔ ገላ ግን ምንም ጠጉር የሌለው ለስላሳ ነው፤ 12 ምናልባት አባቴ ቢዳስሰኝና እንዳታለልኩህ ቢያውቅ በምርቃት ፈንታ እርግማን እንደማተርፍ ታውቂ የለምን?" አላት። 13 እናቱም "ልጄ ሆይ! የአንተ እርግማን በእኔ ላይ ይሁን፤ አሁንም እንደነገርሁህ አድርግ፤ ሄድህ ጥቦቶቹን አምጣልኝ" አለችው። 14 ስለዚህ ሄዶ ጥቦቶቹን አመጣለት እርስዋም ልክ አባቱ እንደሚወደው እድርጋ ጥሩ ወጥ ሠራች፤ 15 የታላቁ ልጅዋን የዔሳውን የክት ልብስ ከተቀመጠበት ቦታ አውጥታ ለያዕቆብ አለበሰችው። 16 የፍየሎቹንም ቆዳ በክንዶቹ ላይና ጠጉር በሌለበት በአንገቱ ላይ አለበሰችው። 17 ያዘጋጀውንም ጥሩ ወጥ ከጋገረችው እንጀራ ጋር ልልጅዋ ለያዕቆብ ሰጠችው።

18 ያዕቆብ ወደ አባቱ ሄደና "አባባ!" አለው፤ እርሱም "እነሆ አለሁ! ለመሆኑ አንተ የትኛው ልጄ ነህ!" አለ። 19 ያዕቆብም "የበኩር ልጅህ ዔሳው ነኝ፤ እነሆ እንዳዘዝከኝ አድርጌአለሁ፤ እንድትመርቀኝ እስቲ ቀና በልና ያመጣሁልህን የአደን ሥጋ ተመገብ" አለው። 20 ይስሐቅም "ልጄ ሆይ! እንዴት ቶሎ ልታገኝ ቻልህ?" አለው። ያዕቆብም "አምላክህ እግዚአብሔር ስለረዳኝ በቶሎ ለማግኘት ቻልሁ" አለው። 21 ይስሕቅም "እስቲ ወደ እኔ ቀረብ በልና ልዳብስህ፤ በእርግጥ አንተ ዔሳው ነህን?" አለው። 22 ያዕቆብም ወደ አባቱ ተጠጋ፤ አባቱም ዳሰሰውና "ድምፅህ የያዕቆብ ድምፅ ይመስላል፤ ክንድህ ግን የዔሳውን ክንድ ይመስላል" አለው። 23 ክንዶቹ እንደ ዔሳው ክንዶች ጠጉራም ስለ ነበሩ ይስሐቅ ያዕቆብን ለይቶ ማውቅ አልቻለም፤ ሊመርቀው ከዝዘጋጀ በኋላ፣ 24 "እርግጥ አንተ ልጄ ዔሳው ነህን?" ሲል እንደገና ጠየቀው፤ እርሱም "አዎ ነን" አለ። 25 ይስሐቅም "ልጄ! በል ከአደንከው ሥጋ አቅርብልኝ፤ ከበላሁም በኋላ እመርቅህለሁ" አለው። ያዕቆብም ምግቡን አቀረበለት፤ የወይን ጠጅም እንዲጠጣ አመጣለት። 26 ከዚህ በኋላ አባቱ ይስሐቅ "ልጄ ሆይ! ቀረብ በልና ሳመኝ" አለው፤ 27 ያዕቆብም ቀርቦ ሳመው። ይስሐቅ የያዕቆብ ልብስ ባሸተተ ጊዜ እንዲህ ሲል መረቀው፣ "እነሆ የልጄ መልካም ሽታ እግዚአብሔር እንደባረከው የእርሻ ሽታ ነው፤
28 እግዚአብሔር ከሰማይ የሚያረሰርሰው ተል ይስጥህ፤ ምድርህን ያለምልምልህ፤ እህልንና የወይን ጠጅህን ያብዛልህ፤
29 መንግሥታት ይገዙልህ፤ ሕዝቦችህም ያገልግሉህ፤ በወንድሞችህ ሁሉ ላይ አለቃ ሁን፤ የእናትህም ልጆች ይስገዱልህ፤ የሚረግሙህ የተረገሙ ይሁኑ፤ የሚመርቁህ የተመረቁ ይሁኑ።"

30 ይስሐቅ ያዕቆብን መርቆ እንዳበቃና ያዕቆብም አባቱን ፊት እንደወጣ ወዲያውኑ ዔሳው ከአደን ተመልሶ መጣ። 31 እርሱም በበኩሉ የጣፈጠ ወጥ ሠርቶ ለአባቱ አቀረበለትና "አባቴ ሆይ እንድትመርቀኝ፣ እስቲ ቀና ብለህ ካመጣሁልህ የአደን ሥጋ ብላ" አለው። 32 ይስሐቅም 'አንተ ማን ነህ?" አለው፤ እርሱም "እኔ የበኩር ልጅ ዔሳው ነኝ" አለ። 33 ይስሐቅም እጅግ ደንግጦ እየተነቀጠቀጠ "ታዲያ አውሬ አድኖ ያመጣልኝ ማን ነበረ? ልክ አንተ ከመምጣትህ በፊት ተመገብሁ የመጨረሻ ምርቃቴንም ሰጠሁት፤ ምርቃቱም ተእርሱ ሆኖ ይኖራል"አለው። 34 ዔሳው ይህን በሰማ ጊዜ ድምፁን ከፍ በማድረግ ምርር ብሎ እያለቀሰ "አባቴ ሆይ! እኔንም መርቀኝ!" አለ። 35 ይስሐቅም "ወንድምህ መጥቶ እኔን በማታለል የአንተን ምርቃት ወስዶብሃል"አለው። 36 ዔሳውም "እርሱ እኔን ሲያሰናክለኝ ይህ ሁለተኛው ነው፤ ያዕቆብ መባሉ ተገቢ ነው፤ ከዚህ በፊት ብኩርናዬን ወሰደብኝ፤ አሁን ደግሞ ምርቃቴን ቀማኝ፤ ታዲያ ለእኔ ያስቀረከው ምንም ምርቃት የለምን? አለው። 37 ይስሐቅም "ቀድሞ ብዬ እርሱን የአንተ ጌታ አድርጌዋለሁ፤ ወንድሞቹ ሁሉ የእርሱ አገልጋዮች እንዲሆኑ አድርጌአለሁ፤ እህልና የወይን ጠጅ እንዲበዛለት አድርጌአለሁ፤ ልጄ ሆይ! እንግዲህ ለአንተ ምን ላደርግልህ እችላለሁ?" አለው። 38 ዔሳውም "አባቴ ሆይ! ምርቃትህ እንዲት ብቻ ናትን? እባክህ እኔንም መርቀኝ" እያለ ለማልቀስ አባቱን ነዘነዘው። 39 ይስሐቅም አንዲህ አለው። "በረከት ከሞላበት ለምለም ምድር ርቀህ ትኖራለህ፤ የሰማይ ጠልም አታገኝም፤
40 በሰይፍም ኅይል ትኖራለህ፤ የወንድምህም አገልጋይ ትሆናለህ፤ በተቃወምከውም ጊዜ ግን ከእርሱ ጭቁና ትላቀቃለህ።"

41 አባቱ ስለመረቀው ዔሳው ያዕቆብን አጥብቆ ጠላው፤ በልቡም "አባቴ በቅርብ ቀን ይሞታል፤ ከዚህ በኋላ ወንድሜን ያዕቆብን እገድለዋለሁ"ብሎ አሰበ። 42 ነገር ግን ርብቃ የዔሳውን ዕቅድ ስለ ሰማች፣ ያዕቆብን ጠርታ እንዲህ አለችው፣ "አድምጠኝ፤ ወንድምህ ዔሳው አንተን በመግደል ሊበቀልህ አስቦአል፤ 43 አሁንም ልጄ ሆይ! የምልህን አድርግ፤ ተነሥተህ በካራን ወደሚገኘው ወደ ወንድሜ ወደ ላባ ሽሽ፤ 44 የወንድምህ ቁጣ እስኪበርድ ድረስ ለጥቂት ጊዜ እዚያው ቆይ፤ 45 ቁጣውም ሲበርድ ያደረግህበትን ነገር ይረሳል፤ ከዚያ በኋላ ሰው ልኬ አስመጣሃለሁ፤ ሁለታችሁም በአንድ ቀን ማጣት አልፈልግም።

46 ርብቃ ይስሐቅን "ዔሳው ባገባቸው በእነዚህ በሖታውያን ሴቶች ምክንያት መኖሬን ጠላሁት፤ ያዕቆብ ደግሞ ከነዚህ ከሒታውያን ሴቶች አንዲቱ ከገባ ለመኖር ይልቅ ሞቴን እመርጣለሁ"አለችው።