25

1 አብርሃም ቀጡራ የምትባል ሌላ ሚስት አገባ፤ 2 እርስዋም ዚምራንን፣ ዮቅሻንን፣ መዳንን፣ ምድያምን፣ ዩሽባቅንና ሹሐን ወለደችለት። 3 ዮቅሻንም ሳባንና ደዳንን ወለደ፤ የዳደንም ዝርያዎች አሹራውያን፣ ሌጡሻውያንና ሌአማውያን ናቸው። 4 የምድያም ልጆች ዔፋ፣ ዔፈር፣ ሐኖክ፣ አቢዳዕና ኤልዳዓ ናቸው፤ እነዚሁ ሁሉ የቁጠራ ዝርያዎች ናቸው። 5 አብርሃም ያለው ሀብት ሁሉ ለይስሐቅ አወረሰው፤ 6 ከሌሎች ሴቶች ለተወለዱትም ልጆች ገና በሕይወት ሳለ ስጦታ ሰጣቸው፤ ከዚህ በኋላ እነዚህ ሌሎች ልጆች ከይስሐቅ ርቀው ወደ ምሥራቅ አገር እንዲሄዱ አደረጋቸው። 7 የአብርሃም ዕድሜ በአጠቃላይ መቶ ሰባ አምስት ዓመት ነበር፤ 8 በዚህም ዐይነት አብርሃም በቂ ዕድሜ አግኝቶ ካረጀ በኋላ ሞተ፤ 9 ልጆቹ ይሰሐቅና እስማኤል ማክጴላ በተባለ ዋሻ ቀበሩት፤ ይህም ዋሻ ከመምሬ በስተምሥራቅ በሒታዊ በጶሐር ልጅ በዔፍሮን እርሻ ውስጥ የሚገኘው ነው። 10 እነሱም አብርሃም ከሒታዊያን ላይ የገዛው የመቃብር ቦታ ነው፤ በዚህ ዐይነት አብርሃም ሚስቱ ሣራ በተቀበረችበት ዋሻ ተቀበረ። 11 አብርሃም ከሞተ በኋላ ልጁን ይስሐቅን እግዚአብሔር ባረከው፤ ይስሐቅ "ብኤርላሐይሮኢ ወይም የሚያየኝ ሕያው አምላክ" ተብሎ በመጠራት ኩሬ አጠገብ ይኖር ነበር።

12 የሣራ አገልጋይ ግብፃዊትዋ አጋር ለአብርሃም የወለደችለትን እስማኤል፤

13 ከዚህ በታች በዕድሜአቸው ቅደም ተከተል ተራ የተዘረዘሩትን ልጆች ወለደ፤ እነርሱም፦ ነባዮት፣ ቄዳር፣ አድብኤል፣ ሚብሣም፣ 14 ሚሽማዕ፣ ዱማ፣ ማሣ፣ 15 ሐዳድ፣ ቴማ፣ ይጡር፣ ናፊሽና ቄድማ ናቸው። 16 እነዚህ የእስማኤል ልጆች ለአሥራ ሁለት ነገዶች ቅድመ አያቶች ነበሩ፤ ስማቸውም በኖሩባቸው ከተሞችና ስፍራዎች ሲጠራ ይኖራል። 17 እስማኤል መቶ ሠላሳ ሰባት ዓመት ሲሆነው ሞተ። 18 የእስማኤል ዝርያዎች ከግብፅ በስተምጅራቅ ወደ አሦር በምትወስደው መንገድ በሐዊላና በሹር መካከል ይኖሩ ነበር። የኖሩበትም ከሌሎቹ የአብርሃም ዝርያዎች ጋር በጥላቻ ተራርቀው ነበር።

19 የአብርሃም ልጅ ይስሐቅ ታሪክ ይህ ነው። አብርሃም ይስሐቅን ወለደ። 20 ይስሐቅ የባቱኤልን ልጅ ርብቃን ሲያገባ አርባ ዓመት ሆኖት ነበር፤ የርብቃ አባት ባቱኤልና ወንድምዋ ላባ በመስጴጦምያ የሞኖሩ ሶሪያውያን ነበሩ። 21 ርብቃ መኻን ስለ ነበረች ይስሐቅ ስለ እርስዋ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤ እግዚአብሔርም ጸሎቱን ስለ ሰማ ርብቃ ፀነሰች፤ 22 የተፀነሱትም መንትያዎች ስለነበሩ እርስ በርሳቸው በማሕፀንዋ ውስጥ ይገፋ ነበር፤ እርስዋም "ይህን ዐይነት በገር ለምን ደረሰብኝ?" በማለት ወደ እግዚአብሔር ለመጸለይ ተነሣሣች። 23 እግዚአብሔርም ያሉት ሁለት ሕዝቦች ናቸው፤ እርስ በርሳቸው የማይስማሙ ሁለት ወገኖች ትወልጃለሽ፤ አንዱም ከሌላው የበረታ ይሆናል፤ ታላቁም ታናሹ አገልጋይ ይሆናል" አላት።

24 የመውለጃዋም ሰዓት በደረሰ ጊዜ ሁለት ወንዶች ልጆች ወለደ። 25 የመጀመሪያው ልጅ መልኩ ቀይ፣ ሰውነቱ ጠጉራም ነበር፤ ስለዚህ ዔሳው ተባለ። 26 ሁለተኛው ልጅ ሲወለድ የዔሳውን ተገረዝ ይዞ በመውጣቱ ያዕቆብ ተባለ፤ ልጆቹ በተወለዱ ጊዜ ይስሐቅ ስልሳ ዓመት ሆኖት ነበር።

27 ሁለቱም ልጆች አደጉ፤ ዔሳው በዱር መዋል የሚወደ ብልኅ አዳኝ ሆነ፤ ያዕቆብ ግን በቤት መዋል የሚወድ ጭምት ሰው ነበር። 28 ይስሐቅ ዔሳውን ይወድ ነበር። ምክንያቱም ዔሳው እያደነ ሥጋ ያበላው ነበር።ርብቃ ግን ያዕቆብን ትንን ነበር። 29 ለዕለታት አንድ ቀን ያዕቆብ ቀይ የምስር ወጥ በመሥራት ላይ እንዳለ ዔሳው ከአደን መጣ፤ በጣም እርቦት ነበር፤ 30 ስለዚህም ያዕቆብ "ከዚህ ከቀይ ወጥ ሰጠኝ" አለው። ኤዶም የተባለውም ነዚሁ ምክንያት ነበር። 31 ያዕቆብም "በመጀመሪያ ብኩርናህን ሽጥልኝ" አለው። 32 ዔሳውም "እኔ በረሀብ መሞቴ ነው፤ ታዲያ ብኩርና ምን ያደርግልኛል?" አለው። 33 ያዕቆብም "እንግዲያውስ ብኩርናህን እንደምትሸጥልኝ መጀመሪያ ማልልኝ" አለው። ስለዚህ ዔሳው ምሎ ብኩርናውን ለያዕቆብ ሸጠ። 34 ከዚህ በኋላ ያዕቆብ የምስሩን ወጥ በእንጀራ አድርጎ ሰጠው፤ ዔሳውም ከበላና ከጠጣ በኋላ ተነሥቶ ሄደ፤ በዚህ ዐይነት ዔሳው ብኩርናውን በመናቅ አቃለላት።