ምዕራፍ 1

1 ሙሴ በዮርዳኖስ ማዶ በምድር በዳ በዮርዳኖስ ወንዝ ሸለቆ ሜዳ በዓረባ፥ በፋራን፥ በጦፌል፥ በላባን፥ በሐጼሮት፥ በዲዛሃብ መካከል ሳሉ፥ ለአስራኤል ሁሉ የተናገራቸው እነዚህ ቃላት ናቸው። 2 በሴይር ተራራ መንገድ ከኮሬብ እስከ ቃዴስ በርኔ ድረስ የአሥራ አንድ ቀን ጉዞ ነው። 3 በአርባኛው ዓመት በአሥራ አንደኛው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን ሙሴ እግዚአብሔር ስለ እነርሱ ያዘዘውውን ሁሉ ለእስራኤል ሕዝብ ነገራቸው። 4 ይህም እግዚአብሔር በሐሴቦን ይኖር የነበረውን የአሞራውያንን ንጉሥ ሴዎንን፥ በአስታዎትና በኤድራይ ይኖር የነበረውንም የባሳንን ንጉሥ ዐግን ከመታ በኋላ ነበር። 5 በዮርዳኖስ ማዶ በሞዓብ ምድር ሙሴ እንዲህ ብሎ እነዚህን መመሪያዎች ይናገር ጀመር፦ 6 እግዚአብሔር አምላካችን በኮሬብ እንዲህ ብሎ ተናገረን፦ በዚህ ተራራ የኖራችሁበት ይብቃችሁ። 7 ጉዞኣችሁን ወደ ኮረብታማው ወደ አሞራውያን አገር ወደ ድንበሮቹም፥ ሁሉ በዓረባም በደጋውና በቆላው፥ በደቡብና በባሕር ዳር ወዳሉ ወደ ከነዓናውያን ምድር፥ ወደ ሊባኖስ ወንዝ ሸለቆ እስከ ታላቁ ኤፍራጥስ ወንዝ ድረስ ሄዱ። 8 እነሆ ምድሪቱን በፊታችሁ አድርጌአለሁ፤ እግዚአብሔር ለአባቶቻችሁ ለአብርሃም፥ ለይስሐቅና ለያዕቆብ፥ ከእነርሱም በኋላ ለዘራቸው ይሰጣቸው ዘንድ የማለላቸውን ምድር ሂዱና ውረሱ። 9 በዚያን ጊዜ እንዲህ ብዬ ተናግሬአችሁ ነበር፦ እኔ በራሴ ብቻዬን ልሸከማችሁ አልችልም። 10 እግዚአብሔር አምላካችሁ አብዝቶአችኋል፥ እነሆም እናንተ ዛሬ እንደ ሰማይ ከዋክብት ብዙ ናችሁ። 11 የአባቶቻችሁ እግዚአብሔር አምላክ ሺህ ጊዜ ሺህ ያድርጋችሁ፤ ተስፋ እንደሰጣችሁም ይባርካችሁ። 12 ነገር ግን እኔ በራሴ ድካማችሁን፥ ሸክማችሁንና ክርክራችሁን እሸከም ዘንድ ብቻዬን እንዴት እችላለሁ? 13 ከእናንተ መካከል ከየነገዶቻችሁ ጥበበኞች፥ አስተዋዮችና አዋቂዎች የሆኑትን ሰዎች ምረጡ፤ እኔም እነርሱን የእናንተ አለቆች አደርጋቸዋለሁ ብዬኣችሁ ነበረ። 14 እናንተም እንዲህ ብላችሁ መለሳችሁ፦ የተናገርከንን ነገር ለማድረግ ለእኛ መልካም ነው። 15 ስለዚህም ጥበበኞችና አዋቂዎች የሆኑትን የነገዶቻችሁን ወሰድሁ፥ በእናንተም ላይ አለቆች እንዲሆኑ የሺህ አለቆች፥ የመቶ አለቆች፥ የአምሳ አለቆች፥ የአሥር አለቆችና ሹማምንት በየገዶቻችሁ አደረግኋቸው። 16 በዚያን ጊዜም ፈራጆቻችሁን እንዲህ ብዬ አዘዝኳቸው፦ በወንድሞቻችሁ መካከል፤ በሰውና በወንድሙ መካከልና በመጻተኛ ላይ በጽድቅ ፍረዱ። 17 በክርክርም ጊዜ ለማንም ፊት አድልዎ አታድርጉ፥ ታላቁን እንደምትሰሙ፥ ታናሹንም ስሙ። ፍርድ የእግዚአብሔር ስለሆነ የሰው ፊት መፍራት አይገባችሁም። ከክርክርም አንድ ስንኳ ቢከብዳችሁ ወደ እኔ አምጡት እኔም እሰማዋለሁ። 18 በዚያን ጊዜም ልታደርጉት የሚገባችሁን ነገር ሁሉ አዘዝኋችሁ። 19 ከኮሬብም ተነስተን፥እግዚአብሔር አምላካችን እንዳዘዘን እንዳያችሁትም በታላቁና እጅግ አስቸጋሪ በሆነ ምድረ በዳ ሁሉ ተጉዘን በተራራማው በአሞራውን አገር ሄድን፥ ወደ ቃዴስ በርኔም መጣን። 20 እኔም እንዲህ አልኋችሁ፦ እግዚአብሔር አምላካችን ወደ ሚሰጠን ወደ ተራራማው አሞራውያን አገር መጣችኋል። 21 እነሆ እግዚአብሔር አምላካችሁ ምድሪቱን በፊታችሁ አድርጎአል፤ የአባቶቻችሁ አምላክ እግዚአብሔር እንዳላችሁ ውጡ፥ ውረሱአት፥ አትፍሩ አትደንግጡም። 22 ከእናንተም ሁላችሁ ወደ እኔ መጥታችሁ እንዲህ አላችሁ፦ ምድሪቱን እንዲሰልሉልንና እናጠቃቸው ዘንድ የሚገባንን የመንገዱንና የምንገባባቸውን ከተሞች ሁኔታ ተመልሰው እንዲነግሩን ከፊታችን ሰዎችን እንድስደድ። 23 ነገሩም ደስ አሰኘኝ፤ ከእናንተም ከየነገዱ ሁሉ አንድ አንድ ሰው፥ አሥራ ሁለት ሰዎችን መረጥሁ። 24 እነርሱም ወደ ተራራማው አገር ሄዱ፥ ወደ ኤሽኮልም ሸለቆ መጥተው ሰለሉአት። 25 እነርሱም ከምድሪቱ ፍሬ በእጃቸው ወሰዱ፥ ወደ እኛም ይዘውት መጡ። እነርሱም ደግሞ፦ እግዚአብሔር አምላካችን የሚሰጠን ምድር መልካም ናት ብለውም አወሩልን። 26 ምድሪቷንም ማጥቃት እንቢ ብላችሁ፥ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ላይ ዐመፃችሁ፥ ። 27 በድንኳናችሁም ውስጥ እንዲህ እያላችሁ አጉረመረማችሁ፦ እግዚአብሔር ስለ ጠላን እንዲያጠፋን በአሞራውያን እጅ አሳልፎ ይሰጠን ዘንድ ከግብፅ ምድር አወጣን። 28 አሁን ወዴት መሄድ እንችላለን? ሕዝቡ ብዙ ነው፥ ቁመቱም ከእኛ ይረዝማል ከተሞቹም ታላላቆች፥ የተመሽጉና እስከ ሰማይም የደረሱ ናችው፥ የዔናቅንም ልጆች ደግሞ በዚያ አየናቸው፤ ብለው ወንድሞቻችን ልባችንን እንዲቀልጥ አደረጉ። 29 እኔም አልኋችሁ፦ አትደንግጡ፥ እነርሱንም አትፍሩአቸው። 30 በፊታችሁ የሚሄደው እግዚአብሔር አምላካችሁ ስለ እናንተ ይዋጋል፥ በፊታችሁም በግብፅና በምድረ በዳ እንዳደረገላችሁ ሁሉ፤ 31 ወደዚህም ስፍራ እስክትመጡ ድረስ በሄድዳችሁበት መንገድ ሁሉ ሰው ልጁን እንደሚሸከም እግዚአብሔር አምላካችሁ እንደ ተሸከማችሁ እናንተ አይታችኋል። 32 ዳሩ ግን እግዚአብሔር አምላካችሁን በዚህ ነገር አላመናችሁትም፤ 33 በፊታችሁም ሆኖ በምትሄዱበት መንገድ ድንኳናችሁን እንድታቆሙ ቦታ እንድታገኙና በሌሊት በእሳት፥ በቀንም በደመና እንድትሄዱ መንገዱን ያሳታችሁ እርሱ ነው። 34 እግዚአብሔርም የቃላችሁን ድምፅ ሰምቶ ተቆጣ፥ ምሎም፥ እንዲህ አለ፦ 35 በርግጥ ለአባቶቻችሁ እሰጣቸው ዘንድ የማልሁላቸውን መልካሚቱን ምድር ከዮፎኒ ልጅ ከካሌብ በቀር ከእነዚህ ሰዎች ከዚህ ክፉ ትውልድ ማንም አያይም። 36 እርሱም እግዚአብህሔርን ፈጽሞ ተከትሎአልና የረገጣትን ምድር ለእርሱና ለልጆቹ እሰጣለሁ ብሎ ማለ። 37 እግዚአብሔርም ደግሞ በእናንተ ምክንያት እኔን ተቆጣኝ እንዲህም አለ፦ አንተ ደግሞ ወደዚያ አትገባም 38 በፊትህ የሚሄድ አገልጋይ የነዌ ልጅ ኢያሱ ወደዚያ ይገባል፥ እርሱም እስራኤላውያን ምድሪቱን እንዲወርሱ ይመራቸዋልና፤ አደፋፍረው። 39 ከዚህም በተጨማሪ፦ ለጉዳት ይዳረጋሉ፥ ዛሬም መልካሙንና ክፉውን መለየት የማይችሉ ናቸው ያላችኋችሁ ታናናሽ ሕፃናታችሁ ልጆቻችሁ እነርሱ ወደዚያ ይገባሉ። ምድሪቱንም ለእነርሱ እሰጣለሁ ይወርሱታልም። 40 እናንተ ግን ተመልሳችሁ በኤርትራ ባሕር መንገድ ወደ ምድረ በዳ ሂዱ። 41 እናንተም፦ እግዚአብሔርን በድለናል፥ እግዚአብሔር አምላክችሁ እንዳዘዘን ሁሉ እንወጣለን፥ እንዋጋማለን ብላችሁ መለሳችሁልኝ። ከእናንተም ሰው ሁሉ የጦር መሣሪያውን ያዘ፥ ወደ ተራራማውም አገር ለመውጣትና ለማጥቃት ተዘጋጀ። 42 እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፦ እኔ በእናንተ መካከል ስለማልገኝ፥ በጠላቶቻችሁ ፊት እንዳትሸነፉ አትውጡ፥ አትዋጉም በላቸው አለኝ። 43 እኔም ተናገርኋችሁ እናንተም አልሰማችሁም። በእግዚአብሔር ትእዛዝ ላይ ዐመፃችሁ፥ አልሰማችሁም በትዕቢታችሁም ወደ ተራራማው አገር ለማጥቃት ወጣችሁ። 44 ነገር ግን በተራራማው አገር ይኖሩ የነበሩ አሞራውያን በእናንተ ላይ ወጥተው እንደ ንብ አሳደዱአችሁ፥ እስከ ሔርማም ድረስ በሴይር መቱአችሁ። 45 ተመልሳችሁም በእግዚአብሔር ፊት አለቀሳችሁ፤ እግዚአብሔር ግን ድምፃችሁን አልሰማም፥ ወደ እናንተም አላዳመጠም። 46 ሁሉም ቀናት በቆያችሁባችሁ ለብዙ ቀን በቃዴስ ተቀመጣችሁ።